Fana: At a Speed of Life!

በሀገር አቀፍ ደረጃ ወጥና ተመሳሳይ የሆነ የታራሚዎች ይቅርታ አሰጣጥ ስርዓት እንዲኖር ለማድረግ የሚያስችል አሰራር ሊዘረጋ መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 1 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ የክልሎችንና የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አሰራር፣አደረጃጀትና፣አፈፃፀም ምን እንደሚመስል በመዳሰስ በሀገር አቀፍ ደረጃ ወጥና ተመሳሳይ የሆነ የይቅርታ አሰጣጥ ስርዓት እንዲኖር የሚያስችል ጥናት ማካሄዱን አስታወቀ፡፡

በኢፌዴሪ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ የይቅርታ ቦርድ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ዘለቀ ደላሎ እንደገለፁት ፥በ2011 ዓ.ም በነበረዉ ሀገር አቀፍ የጋራ መድረክ ላይ የታራሚዎች የይቅርታ አሰጣጥ ስርዓቱ እንደየ ክልሎች ነባራዊ ሁኔታ የተለየ አሰራርና አፈፃፀም መኖሩ ችግር እየፈጠረ መሆኑ ታምኖበት ሀገር አቀፍ ወጥና ተመሳሳይ የይቅርታ አሰጣጥ ስርዓት ሊኖር እንደሚገባ በመታመኑ ጥናቱ እንደተካሄደ ገልፀዋል፡፡

በጥናቱም አንዱ ክልል ላይ ይቅርታ የሚያሰጥ ጉዳይ ሌላዉ ክልል ላይ የማያሰጥ ሆኖ መገኘቱንና በዚህም ምክንያት በታራሚዎች ላይ ቅሬታን ከመፍጠሩ በተጨማሪ ሰዎች በፍትህ ስርአቱ ላይ እምነት እንዲያጡ አድርጓል ብለዋል፡፡

በመርህ ደረጃ የወንጀል ህግንና እሱን ተከትሎ የሚደረጉ ተግባራትን የማዉጣት ስልጣንና ሀላፊነት የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ እንደነበረ ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ክልሎች ያልተፈቀደላቸዉን ስልጣንና ሃላፊነት ተከትለዉ የሚሰሩትን ስራ ለማስቀረትና ህገ መንግስታዊ፣ ወጥ የሆነ የይቅርታ አሰጣጥ አዋጅ በፌዴራል ደረጃ ወጥቶ ክልሎችም በዉክልና ወስደዉ በተመሳሳይ ሁኔታ ታይቶ እንዲሰራ ይደረጋል ብለዋል።
እንዲሁም የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት የተጠናዉ ጥናት በሀገር አቀፍ መድረክ ላይ ቀርቦ ዉይይት ተደርጎበት ከፀደቀ በኋላ ወደ ስራ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በተያያዘም የሞት ፍርደኞችን ጉዳይ በተመለከተም ግልፅና ወጥ የሆነ አሰራር እንዲኖር ለማድረግ የሚያስችል ጥናት መካሄዱን የገለፁት ሀላፊዉ የሞት ፍርደኞች እጣ ፈንታ ምንድን ነዉ፣እንዴት ይያዙ፣ጉዳያቸዉ እንዴት ሪፖርት ይደረግና አጠቃላይ መስፈርቶቹስ ምን መሆን አለባቸዉ የሚሉ ጉዳዮች ላይ ወጥ የሆነ አሰራር እንዲኖር ለማድረግ ጥናት መካሄዱንም አቶ ዘለቀ ተናግረዋል፡፡

ለውጡን ተከትሎ ይቅርታ ከተደረገላቸዉ 41 ታራሚዎች ዉጭ በሁሉም ማረሚያ ቤቶች 147 የሞት ፍርደኞች እንደሚገኙ ከፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቢ ህግ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.