ኢ/ር ታከለ ኡማ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 4 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ጋር ተወያይተዋል።
በዚህ ወቅትም ኢንጂነር ታከለ የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ ላይ በቅርስት በመምዝገቡ የተሰማቸውን ደስታ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ገልጸዋል።
የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊና ባህላዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከበርና የቱሪስቶችን ቀልብ እንዲስብ በሚያደርግ መልኩ እንዲከናወን የከተማ አስተዳደሩ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።
በቀጣዩ ሳምንት የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት መመዝገቡን አስመልክቶ በሚሊኒየም እዳራሽ ለሚዘጋጀውና ሁሉም የሃይማኖት መሪዎች ለሚገኙበት መርሃ ግብር ስኬትም ከተማ እስተዳድሩ ድጋፍ የሚያድርግ መሆኑን ጠቁመዋል።
የከተማ አስተዳደሩ የጀመረውንና የቤተ ክርስቲያን የረጅም ጊዜ ጥያቄ የሆነው የይዞታ ማረጋገጫ የመስጠት ጉዳይም በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥል መናገራቸውን ከከንቲባ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የሁሉም ኢትዮጵያውያን ሃብት የሆነው የጥምቀት በዓል በደመቀ ሁኔታ እንዲከበር ቤትክርስቲያኒቱ እና የከተማ እስተዳደሩ በቅንጅት እንደሚሰሩም ተመላክቷል።