ኢትዮጵያዊያን ወጣቶችን የተሻለ ተጠቃሚየሚያደርግ ”ዩዝ ኮኔክት ኢትዮጵያ” የተሰኘ ሀገራዊ ፕሮግራም ሊጀመር ነው
አዲስ አበባ፣ታህሳስ 9፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያዊያን ወጣቶችን የተሻለ ተጠቃሚ የሚያደርግ ”ዩዝ ኮኔክት ኢትዮጵያ” የተሰኘ ሀገራዊ ፕሮግራም በይፋ ሊጀመር ነው፡፡
ሀገራዊ ፕሮግራሙን በይፋ ለማስጀመር ዝግጅቱን ማጠናቀቁን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የፕሮግራሙን መጀመር አስመልክቶ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በሰጠው መግለጫ ላይ “ዩዝ ኮኔክት ኢትዮጵያ” የወጣቶችን የእርስ በርስ ግንኙነትና ትስስር ከማሳደግ ጎን ለጎን ያለባቸውን ዘርፈ ብዙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በመፍታት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋል ተብሏል፡፡
እንዲሁም ለሀገራቸውና ለአህጉራቸው ሰላም፣ ዕድገትና ብልጽግና ገንቢ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ለማስቻል ያለመ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ፕሮግራሙ ከወጣቶች ስብዕና ልማት፣ ከስራ ፈጠራ፣ ከበጎ ፈቃደኝነትና ማህበራዊ አገልግሎት፣ ከሰላምና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እንዲሁም ከቴክኖሎጂ ምርምርና ስርጸት ጋር የተያያዙና ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታቸው ከፍ ያሉ ሃሳቦችን ማዕከል አድርጎ የሚተገበር መሆኑ ተገልጿል፡፡
የተነደፉ የመንግስት ፖሊሲዎች የፕሮግራሙ ዓላማዎች ስራ ላይ እንዲውሉና የሚፈለገውንም ውጤት እንዲያመጡ የበኩሉን እገዛ እንደሚያደርግና በአስፈጻሚ አካላት ዘንድም የተሻለ መነቃቃት እንደሚፈጥር ሚኒስትሯ ወይዘሮ ያለም ጸጋይ ገልጸዋል፡፡
ዩዝ ኮኔክት ኢትዮጵያ የተነሳበት ዓላማ እውን እንዲሆን ወጣቶችን ጨምሮ ወጣቶችን ማዕከል አድርገው የሚንቀሳቀሱ ማህበረሰብ – ተኮር ድርጅቶች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የግል ሴክተሮች፣ መላው ህብረተሰብና በጋራ እንዲረባረቡ ሚኒስትሯ ጥሪ አቀርበዋል፡፡
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ህይወት ኃይሉ በበኩላቸው ዩዝ ኮኔክት ፕሮግራም የዩዝ ኮኔክት አፍሪካ ኢኒሼቲቭ አካል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከፈረንጆቹ በ2012 ዓ.ም ጀምሮ በሩዋንዳ መንግስት በተለይም በሀገሪቱ ርዕሰ ብሄር ፖል ካጋሚ አስተባባሪነትና በተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት (UNDP) አጋርነት መጀመሩንና በአሁኑ ወቅትም 14 የአፍሪካ ሀገራት እየተገበሩት ይገኛሉ ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያም ተሞክሮውን በመውሰድ ከነባራዊ ሁኔታ ጋር በተጣጣመና የሀገሪቱን ወጣቶች ተጠቃሚነት ሊያረጋግጥ በሚያስችል መልኩ ፕሮግራሙን ለመተግበር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አድርጋለች ነው የተባለው፡፡
ሚኒስትሯ አክለውም ፕሮግራሙን ወደ ሙሉ ትግበራ ለማሸጋገርም ወጣቶችና ባለድርሻ አካላት በተሳተፉበት አግባብ እቅድ እንደሚዘጋጅ፣ አፈጻጸሙንም የሚከታተል ስትሪንግ ኮሚቴ በየደረጃው እንደሚቋቋምና በፕሮግራሙ ዙሪያ የህብረተሰቡን የመረጃ ተደራሽነት ለማሳደግ ከቴክኖሎጂ ጋር የማስተሳሰር ስራ ይሰራል ብለዋል፡፡
“ዩዝ ኮኔክት ኢትዮጵያ” ፕሮግራም ከታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች በይፋ እንደሚጀመር የጠቆሙት ሚኒስትሯ በቀጣይም በጽንሰ-ሃሳቡና በዓላማው ዙሪያ ወጣቱንም ሆነ በየደረጃው የሚገኙ አስፈጻሚ አካላትንና የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ የሚያግዙ ሰፋፊ የግንዛቤና ንቅናቄ ስራ እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡
በአዲስ አበባ በአፍሪካ የአመራርነት ጥናት ማዕከል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ ታደሰ በበኩላቸው እንዲህ ዓይነቱ ፕሮግራም ወጣቶችን ብቻ ሳይሆን የመንግስት አካላትን፣ የማህበራዊ ጥናት ፖሊሲ አርቃቂዎችን፣ ስራ ፈጣሪዎችን፣ ባለሃብቶችን፣ ታዋቂና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችንና በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ ሙያተኞችን በአንድ የሚያስተሳስርና የሚያገናኝ መድረክ ነው፡፡