የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል በአፋር ክልል በጎርፍ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎችን ጎበኙ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል የተመራ ቡድን በአፋር ክልል በጎርፍ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች የዘዋውረው ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱም በአፋር ክልል በአዋሽ ወንዝ ከመጠን ባለፈ መጨመር ምክንያት ህይወታቸውና ንብረታቸው ለአደጋ የተጋለጡ ዜጎቻችንን ሁኔታ ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
ወንዙ ከ30 ዓመት ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ በከፍተኛ መጠን በመጨመሩ ምክንያት በተለይም ከቆቃና ከከሰም ግድብ አቅም በላይ የሆነው ውሃ ከአዋሽ እስከ አፋምቦ ድረስ በአካባቢው ማህበረሰብ ላይ ጉዳት ማድረሱ ይታወቃል።
የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ጉብኝቱን አስመልክቶ በፌስቡክ ገፃቸው ባወጡት መረጃ፥ የክልልና ፌደራል መንግስቱ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል በማሰብ ቀድሞ ሰፊ ርብርብ ማድረጉ እንደተጠበቀ ሆኖ አደጋው ከተገመተው በላይ ሰፋ ብሎ በመምጣቱ ችግሩ ሊከፋ ችሏል ብለዋል።
አሁንም በርካታ ቤተሰቦች የአስቸኳይ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ከመኖራቸውም በላይ ቀጣይ ጉዳት እንዳይደርስም የተጀመረውን እርዳታ አጠናክሮ ከመቀጠል ጎን ለጎን ወንዙን ወደ ተለመደው ፍሰቱ ለመመለስ የተቀናጀ ርብርብ እንደሚጠይቅም አስታውቀዋል።
የክልሉ መንግስት፣ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ መከላከያ ሰራዊት፣ የፌደራል ፖሊስ አባላት፣ የአደጋ ስጋት መከላከል አመራሮችና ሰራተኞች በአጠቃላይ አደጋው ከደረሰበት ጊዜ አንስቶ በህይወት አድንም ይሁን በተለያየ መንገድ አደጋውን የመከላከል ተግባራት ሰፊ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝም ገልፀዋል።
“በዚህ የነፍስ አድን ተግባር የተረባረባችሁና አንድም የህይወት ዋጋ እንዳይከፈል ያስቻላቹ ወገኖቼ በሙሉ የላቀ አክብሮትና ምስጋናዬ ይድረሳችሁ” ብለዋል የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል።
በቀጣይም አደጋውን በዘላቂነት ደረጃ በደረጃ ለመፋታት የአጭር የመካከለኛና የረጅም ጊዜ እቅዶችን በማስቀመጥ የተጀመረው ጥረት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሁሉ በመቀናጀት ከግብ ለማድረስ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።
ችግሩን ለመቋቋምና ህብረተሰቡን መልሶ ለማቋቋም አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለንም ብለዋል።
በተጨማሪም ሚኒስትሯ በመተሓራ እና ዙርያዋ በሚገኙ ወረዳዎች በጎርፍ ጉዳት የደረሰባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በሚገኙባቸው ጊዜያዊ መጠለያ ጣብያዎች ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡
በመንግሥት የተጀመረው ሁለንተናዊ ጥረት ከአጭር ከመካከለኛና ከረዥም ጊዜ አንፃር ዜጎችን ወደ ተረጋጋ ህይወት እስኪመለሱ የሚከናወኑ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
እናቶች ህፃናት በእድሜ የገፉ አባቶች፤ የሚያጠቡና ነፋሰ ጡር ሴቶች የበለጠ ትኩረት ያስፈልጋቸዋል ያሉት ሚኒስትሯ፤ በፍጥነት የሰብአዊ እርዳታዎችን የማድረስና የማቋቋም ተግባር ውስጥ በመግባት የተሄደበት ጥረት ከዳር እስኪደርስ ርብርቡ እንደሚቀጥልም በፈስቡክ ገፃቸው ላይ አስፍረዋል።
ሚኒስትሯ ይህ ሁኔታ የሚያልፍ ነዉ ፤ስንተባበር የማንሻገረው ዳገት የማንወጣው ተራራ አይኖርም ነው ያሉት።