በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በህገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ ከ2 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር በላይ ተያዘ
አዲስ አበባ፡ መስከረም 6 ፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በህገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ ከ2 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር በላይ መያዙን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
በክልሉ በሚገኙ 4 የተለያዩ ኬላዎች በተደረገ ፍተሻ 2 ሚሊየን 370 ሺህ ብር መያዙንን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አብዱልአዚም መሀመድ ገልፀዋል።
በክልሉ ኩርሙክ ወረዳ ሱዳን ድንበር አካባቢ በግለሰብ ሲዘዋወር የነበረ 600 ሺህ ብር የሚሆን ገንዘብ ሲያዝ በመተከል ዞን ጉባ ወረዳ ማንኩሽ ኬላ 300 ሺህ እንደተያዘ ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽነር አብዱልአዚም አክለውም፣ በክልሉ አሶሳ ከተማ አሶሳ ኬላ 700 ሺህ ብር እና አሶሳ ዞን ቡልድግሉ ወረዳ ጎንቆሮ ኬላ ደግሞ 770 ሺህ ብር እንደተያዘ መናገራቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የክልሉ መንግስት መሠል ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመቆጣጠር ክትትሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት ኮሚሽነር አብዱልአዚም፣ ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ትብብር ማድረጉን አጠናክሮ እንዲቀጥለም ጥሪ አቅርበዋል፡፡