Fana: At a Speed of Life!

ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በጎርፍ ለተጎዱ ዜጎች ድጋፍ ለማድረግ ሰመራ ገቡ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የአዲስ አበባ ከተማ አሰተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በአፋር ክልል በጎርፍ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ ለማድረግ ሰመራ ከተማ ገብተዋል።
ምክትል ከንቲባዋ ሰመራ ሱልጣን አሊሚራህ ሃንፈሬ አየር ማረፊያ ሲደርሱ የአፋር ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አወል አርባን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና የተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎች አቀባባል እንዳደረጉላቸው ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬቴሪያት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአፋር ክልል በወንዞች ሙላት ሳቢያ በተፈጠረው የጎርፍ መጥለቅለቅ ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች በአይነት 10 ሚሊየን፣ በገንዘብ 2 ሚሊየን በድምሩ 12 ሚልየን ድጋፍ ለማድረግ የከተማው ካቢኔ መወሰኑ ይታወሳል።

ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ድጋፉን የክልሉ ፕሬዝዳንት  አቶ አወል አርባ አና ሌሎች አመራሮች በተገኙበት አስረክበዋል።

ወይዘሮ አዳነች ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት በክልሉ በደረሰው የጎርፍ አደጋ የሰው ህይወት ባይጠፋም በደረሰው የመፈናቀል እና የዜጎች መንገላታት ማዘናቸውን ገልጸዋል።

በደረሰው አደጋ ለተጎዱ እና ከመኖሪያ ቄያቸው ለተፈናቀሉ የአፋር ወገኖቻችን የተደረገው ድጋፍ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት የዘለቀውን የመደጋገፍና የመተባበር እሴቶችችንን የሚያዳብር እና አብሮነትን የሚያረጋግጥ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

በአደጋው የተፈናቀሉ ዜጎች ህይወታቸውን በዘላቂነት እንዲመሩ የከተማ አስተዳደሩ ከክልሉ መንግስት ጋር በመተባበር አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉያደርጋል ነው ያሉት።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ሐጂ አወል አርባ በበኩላቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጎርፍ መጥለቅለቅ የተጎዱ የክልሉ ዜጎችን ለመደገፍ ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል፡፡

ድጋፉ አዲስ አበባ የሁሉም ዜጋ መመኪያ መሆኗን በተግባር ያረጋገጠ ነው ያሉት ሃጂ አወል የክልሉ መንግስት ዜጎችን ህይወታቸውን በዘላቂነት እንዲመሩ ለማድረግ በሚሰራው ስራ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከጎናቸው እንደሚቆም ያላቸውን  እምነት ገልጸዋል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.