የመተከል ዞን ለሚቀጥሉት ሶስት ወራት በኮማንድ ፖስት ስር ይቆያል -የክልሉ መንግስት
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 13 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ከአመት በፊት የአካባቢውን ሠላም ለማጠናከር የተዋቀረው ኮማንድ ፖስት ለሚቀጥሉት ሶስት ወራት እንዲቀጥል መወሰኑ ተገለጸ።
የክልሉ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መለሰ በየነ እንዳስወቁት በክልሉ ከአንድ ዓመት በፊት የተዋቀረው ኮማንድ ፖስት ለቀጣይ ሶስት ወራት የአካባቢውን ሠላም የማስመለስ ስራውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ተወስኗል።
“ኮማንድ ፖስቱ በክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር እንደሚመራ ገልጸው፤ ከአጎራባች አማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች፣ ከሃገር መከላከያ ሠራዊት፣ በፌደራል ፖሊስ እና በየደረጃው ከሚገኙ የጸጥታ ሃይሎች ጋር በቅንጅት ይሠራል” ብለዋል።
በዚሁ መሰረት በመተከል ዞን የሚገኙ ግጭት በተደጋጋሚ የተከሰተባቸው ጉባ፣ ቡለን፣ ዳንጉር እና ወምበራ ወረዳዎች የሚከናወኑ የኮማንድ ፖስቱ አጠቃላይ እንቅስቃሴዎች በሃገር መከላከያ ሠራዊት በበላይነት እንደሚከናወኑ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
“ሌሎች በዞኑ የሚገኙ ፓዌ፣ ድባጤ እና ማንዱራ ወረዳዎች ያለው እንቅስቃሴ ደግሞ በኮማንድ ፖስቱ ስር ሆነው አፈጻጸሙ በወረዳ አመራሮች ክትትል ይደረግበታል” ብለዋል።
“ከዚህ ቀደም በዞኑ የተጣሉ የጦር መሳሪዎችን እና ማናቸውንም ስለታማ ነገሮችን ይዞ መንቀሳቀስ እንደተከለከለ ይቀጥላል” ብለዋል።
በየኬላዎችም ጠንካራ ፍተሻዎች እንደሚከናወኑ ጠቅሰው፤ እንደ አስፈላጊነቱ የሰዓት እላፊዎችም በክልከላው ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
በተለይም በግጭት የተፈናቀሉትን ሙሉ በሙሉ ወደ ቀያቸው በመመለስ በዘላቂነት ማደራጀት በኮማንድ ፖስቱ እንደሚከናወን አስታውቀዋል።
በቁጥጥር ስር ያልዋሉ የጥፋት ሃይሎች ከገቡበት ገብቶ አድኖ መያዝ ሌላው የኮማንድ ፖስቱ ተግባር እንደሆነ ገልጸው፤ ስራውን ውጤታማ ለማድረግ ኮማንድ ፖስቱ ህብረተሰቡ ዋነኛ አጋር አድርጎ እንደሚሠራ ተናግረዋል።
ይህን ለማሳካት ከዚህ ቀደም በየአካባቢው የተጀመሩ ህዝባዊ የውይይት መድረኮች በከፍተኛ አመራሩ በግንባር ቀደም ሃላፊነት እንደሚቀጥሉ አቶ መለሰ አብራርተዋል።
ባለድርሻ አካላት በኮማንድ ፖስቱ የተቀመጡ ክልከላዎችን ከማክበር ባሻገር አስፈላጊውን መረጃ ከመስጠት ጀምሮ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አቶ መለሰ ጥሪ አቅርበዋል።