የቱርክ ፕሬዚዳንት ሀገራቸው አዲስ ስደተኛ ማስተናገድ እንደማትችል ገለጹ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የቱርክ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጠይብ ኤርዶኻን ሀገራቸው ከሶሪያ የሚፈልሱትን የስደተኖች ማእበል ማስተናገድ እንደማትችል ገለጹ።
ፕሬዚዳንቱ ይህንን የገለጹት በሰሜን ምእራብ ሶሪያ ኢድሊብ ግዛት የተፈፀመውን የቦምብ ፋንዳታ ተከትሎ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሶሪያውያን ወደ ቱርክ ድንበር መሸሻቸውን ተከትሎ ነው።
ቱርክ እስካሁን 3 ነጥብ 7 ሚሊየን የሶሪያ ስደተኞችን በማስተናገድ ከአለም ትልቁን የስደተኖችን ቁጥር አስተናገደች ሀገር ናት ተብሏል።
እስከ ሶስት ሚሊየን የሚደርሱ ሰዎች የሚኖሩት የሶሪያዋ ኢድሊብ ግዛት አሁንም ድረስ ፕሬዚዳንት ባሻር አልአሳድን በሚቃወሙ አማጽያንና ጃሂዲስቶች እጅ መሆኗ ተነግሯል፡፡
የቱርክ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጠይብ ኤርዶኻን በሶሪያ ያለውን አመፅ ማስቆም ካልተቻለ የአውሮፓውያኑ የ2015ቱ የስደተኞች ቀውስ ድጋሜ ሊከሰት ይችላል፤ ይህ ችግር ሁሉንም የአውሮፓ ሀገራት ያሰጋል ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ለመወያየት የቱርክ ልዑካን ቡድን ዛሬ ወደ ሞስኮ ለመሄድ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
ሩሲያ እና ቱርክ ባለፈው ነሐሴ ወር የሶሪያ መንግሥት በኢድሊብ ግዛት የሚደርሰውን ጥቃት ለማቆም የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ከደረሱ ወዲህ በአካባቢው ውዝግብ እና ድብደባ አሁንም የዕለት ተዕለት ክስተት መሆናቸው ነው የተነገረው።
ምንጭ፡- ቢ.ቢ.ሲ