ትልልቅ የሙስና ወንጀል ተሰርቶባቸዋል ተብለው በተጠረጠሩ ተቋማት ላይ የተደረገው ጥናት ተጠናቋል – ብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት
አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 13 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ትልልቅ የሙስና ወንጀል ተሰርቶባቸዋል ተብለው በተጠረጠሩ ተቋማት ላይ የተደረገው ጥናት መጠናቀቁን የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት አስታወቀ።
የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ደመላሽ ገብረሚካኤል ባለፉት ስድስት ወራት ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ እና የገንዘብ ዝውውርን ለመቆጠጣር የሚያስችሉ መረጃዎችን ለሚመለከተው አካል በማቅረብ የተሳካ ስራ መስራቱን ተናግረዋል።
የኢኮኖሚ አሻጥሮችን በመከላከል በኩል በግብር ስወራ፣ ኮንትሮባንድ እና የጨው ምርት ሽያጭ አሻጥር ላይ አጣርቶ መረጃ ማቅረቡንም ነው የተናገሩት።
ከግብር ስወራ እና የመንግስት ሀብት ምዝበራ አንፃር ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ ሀብት ለማዳን ያስቻለ ስራ መሰራቱንም ገልጸዋል።
የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ከፍተኛ የሙስና ወንጀል ተፈፅሞባቸዋል በተባሉ የመንግስት ተቋማት ላይ ጥናቶችን አጠናቆ ለመንግስት ማስረከቡንም አስታውቀዋል።
በዳዊት መስፍን