ምክር ቤቱ የኢትዮ-ጅቡቲ የተፈጥሮ ጋዝ ቧንቧ መስመር ዝርጋታ ስምምነትን አፀደቀ
አዲስ አበባ፣ታህሳስ 14፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኢትዮጵያና በጅቡቲ መንግስታት መካከል የተፈጥሮ ጋዝ ቧንቧ መስመር ማስተላለፊያን ለመዘርጋት የተደረሰውን ስምምነት እና የፌዴራል ማረሚያ ቤት ረቂቅ አዋጆችን አፀደቀ።
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 7ኛ መደበኛ ስብሰባውን በዛሬው እለት አካሂዷል።
ምክር ቤቱ በዛሬው መደበኛ ስብሰባውም የፌዴራል ማረሚያ ቤት ረቂቅ አዋጅን ተመልክቷል።
በዚህ ወቅት ከህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቶ አበበ ጉዴቦ የፌዴራል ማረሚያ ቤት ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፥ ቋሚ ኮሚቴው ረቂቅ አዋጁ ላይ ከፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግና ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ጋር እንዲሁም ከህዝብ ክንፍ ጋር በቂ ውይይት መደረጉን አስታውቀዋል።
ረቂቅ አዋጁ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የኢፌዴሪ ህገ መንግስት እና ህገ መንግስቱን መሰረት አድርገው የወጡ ህጎች እንዲሁም ሀገሪቱ ፈርማ ባፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች መሰረት እስረኞችን በመጠበቅ እና በማነፅ የተጣለበትን ሃላፊነት እንዲወጣ የሚያስችል መሆኑን አስታውቅዋል።
እንዲሁም ረቂቅ አዋጁ የማረሚያ ቤቶችን አደረጃጀት የተሻለ ለማድረግ ፣የማረሚያ ቤት ፖሊስ አባላት ከተልዕኳቸው ጋር የሚመጣጠን የማረሚያ ቤት ፖሊስ የሚል ስያሜ አግኝተው ደረጃውን እና ሃላፊነቱን የሚገልፅ ማእረግ እና ምልክት እንዲኖራቸው የሚያደርግ መሆኑንም ገልፀዋል።
በተጨማሪም ማረሚያ ቤቶች የእስረኞችን ሰብአዊ መብት በማክበር እንዲሁም የእስረኞቹ ግላዊ ሁኔታ በሚጠይቀው የፍርድ አፈጻጸም እና እርማት ስልቶችን ተግባራዊ በማድረግ እውቀትና ክህሎትን አዳብረው ከህብረተሰቡ ጋር የሚቀላቀሉበትን ስርዓት ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰዋል።
የምክር ቤቱ አባላትም የፌዴራል ማረሚያ ቤት ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተወያዩ በኋላ አዋጁን በሙሉ ደምጽ አጽድቀዋል።
በመቀጠልም ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና በጅቡቲ ሪፐብሊክ መንግስታት መካከል የተፈጥሮ ጋዝ ቧንቧ መስመር ለማስተላለፍ የተደረሰውን ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅ ተመልክቷል።
ከተፈጥሮ ሀብት፣ መስኖና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ወይዘሮ ፈቲያ የሱፍ፥ ረቂቅ አዋጁ ላይ በሰጡት ማብራሪያ ስምምነቱ ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ጋዝ በሚዘረጋው ቧንቧ በማስተላለፍ ጋዙን ለሚጠቀሙ ሀገራት በመሸጥ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት የሚያስችላት መሆኑን ገልፀዋል።
የቧንቧ መስመሩ ባለቤት ኢትዮጵያ መሆኗን በረቂቁ ላይ በግልፅ ፣ በሀገራቱ መካከል የተደረሰው የተፈጥሮ ጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧ መስመር ዝርጋታ ስምምነት ዓለም አቀፍ የስምምነት ደረጃ መስፈርትን የሚያሟላ እና ከዚህ በፊት በሀገራቱ መካከል የነበሩ ስምምነቶችን የሚያጠናክር መሆኑን ገልፀዋል።
ይህንን ተከትሎም የምክር ቤቱ አባላት በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና በጅቡቲ ሪፐብሊክ መንግስታት መካከል የተፈጥሮ ጋዝ ቧንቧ መስመር ለማስተላለፍ የተደረሰው ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅን በሙሉ ደምጽ አፅድቀዋል።
ምክር ቤቱ በመቀጠልም በውጭ ሀገራት ለተሰጡ የግልግል ዳኝነት ውሳኔዎች እውቅና የመስጠት እና የመፈጸም ስምምነትን ለማጽደቅ የቀረበ ረቀቅ አዋጅን ተመልክቷል።
የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ደኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በረቂቅ አዋጁ ላይ በሰጡት ማብራሪያ፥ የረቂቅ አዋጁ ዓላማ የግልግል ዳኝነት እና ስምምነት በአባል ሀገራት ፍርድ ቤቶች እውቅና እንዲኖራቸው እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረጉ ስምምነቶች የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስጠብቁ ለማድረግ የሚረዳ መሆኑን እና የውጭ ሀገራት ኢንቨስትመንት እና ንግድን እንደሚያበረታታም አስረድተዋል።
የምክር ቤቱ አባላትም በረቂቅ አዋጁ ላይ በሰጡት አስተያየት ኢትዮጵያ ስምምነቱን ብትቀበለው እና ብታፀድቀው በሀገሪቱ የሚሰጡ የግልግል ዳኝነት ውሳኔዎች በሌሎች ሀገራት ተፈፃሚ እንዲሆኑ እንዲሁም በሌሎች ሀገራት የተወሰኑ ውሳኔዎች በኢትዮጵያ እንዲፈፀሙ በማድረግ ነገሮችን ለማቀላጠፍ እና ለማቃለል እንደሚረዳ ገልፀዋል።
ከአስፈፃሚ ጋር በተያያዘ በረቂቅ አዋጁ አስፈፃሚው ጠቅላይ አቃቤ ህግ ከሌሎች አካላት ጋር የሚለው ለምን በዝርዝር ለፖሊስ እና ፍርድ ቤት በሚል በግልፅ የሚል ጥያቄ የምክር ቤቱ አባላት አቀርበዋል።
ምክር ቤቱም ረቂቅ አዋጁን ለዝርዝር እይታ በዋናነት ለህግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንዲሁም በተባባሪነት ለውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ መርቷል።
በሙለታ መንገሻ