Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ክልል በመንገድ ዘርፍ በተከናወኑ ተግባራትና ተግዳሮቶች ዙሪያ ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 15፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በደቡብ ክልል በመንገድ ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት፣ የተገኙ ዉጤቶች ፣ ተግዳሮቶች እና የቀጣይ አካሄዶችን በተመለከተ በሃዋሳ ከተማ ዉይይት ተካሄደ፡፡

በውይይት መድረኩ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ዕርስቱ ይርዳዉ ፣የትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ፣ የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጅነር ህይወት ሞሲሳ እና የኢትዮጽያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሃብታሙ ተገኝ እንዲሁም የፌደራል፣ የክልል እና የዞን አመራሮች ተገኝተዋል፡፡

የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ዕርስቱ ይርዳዉ በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር በመንገድ ዘርፍ በክልሉ ብሎም በሃገር አቀፍ ደርጃ ተጨባጭ ለዉጥ መመዝገቡን አንስተዋል፡፡

ይህም ዉጤት ተጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ የሚታዩ ተግዳሮቶችን በመለየት የመፍትሄ አቅጣጫ አስቀምጦ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚስፈልግ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል፡፡

የትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በበኩላቸው የመንገድ ግንባታ ከፍተኛ መዋለ ንዋይ የሚጠይቅ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

መንገድ ከፍተኛ ፋይዳ ያለዉ በመሆኑ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ተጀምሮ መጠናቀቅ እንዲችል በዘርፉ ከወሰን ማስከበር እና ከጸጥታ አንፃር እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመቅርፍ ሁሉም የባለድርሻ አካላት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡

የዚህ መድርክ ዋና ዓላማ በከልሉ በሚከናወኑ የመንገድ ፕሮጀክቶች ላይ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን በዋነኛነት የወሰን ማስከበር እና አልፎ አልፎ ከፀጥታ ጋር የተያያዙ ችግሮች በመለየት እና መፍትሄ በማስቀመጥ በዘርፉ የላቀ ዉጤት ማስመዘገብ የሚቻልበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በዚህም በግንባታ ሂደት ላይ ያሉ የመንገድ ፕሮጀክቶች በዝርዝር ቀርበዉ በስፋት ዉይይት ተካሂዶባቸዋል ነው የተባለው፡፡

የኢትዮጽያ መንገዶች ባለስልጣንም ከጥራትና ፕሮጀክቶች መዘግየት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመቅርፍ ጠንካራ የክትትል ስርአት በመዘርጋት እየተሰራ መሆኑ ተነግሯል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በአዉሮፓ ህብረት ድጋፍ የሁሉም ክልሎች የመንገድ ባለስልጣን መስሪያ ቤቶች አቅም ለማጎልበት ይቻል ዘንድ እየተካሄደ ያለዉ ጥናት በአማካሪ ድርጅቱ በኩል መቅረቡን ከባለስልጣኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.