Fana: At a Speed of Life!

16ኛው ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ቀን በአዲስ አበባ እየተከበረ ነው

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 16፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ16ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ15ኛ ጊዜ በአዲስ አበባ እየተከበረ ነው።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ፣ የፌደራል የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አየልኝ ሙሉዓለም፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ፖለቲከኞች፣ አርቲስቶች፣ የማህበረሰብ አንቂዎችን ጨምሮ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ቀኑ “መልካም ስነ ምግባርን በመገንባት፣ ሙስናን በመታገል ዘላቂ ሰላምና ልማታችንን እናረጋግጥ” በሚል መሪ ሀሳብ ነው እየተከበረ የሚገኘው።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፊልምና ቲያትር ክፍል ተማሪዎች የተዘጋጀና በፀረ ሙስና ትግል ላይ ያተኮረ አጭር ጭውውት ቀርቧል።

በዝግጅቱ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በፀረ ሙስና ትግሉ አርዓያ ለሆኑ ተቋማትና ግለሰቦች የእውቅና አሰጣጥ መርሃ ግብር የሚካሄድ ሲሆን፥ በበዓሉ ዙሪያ አነቃቂ የሆነ ንግግርም በመጋቢ ሀዲስ እሸቱ የሚቀርብ ይሆናል።

“ሙስናን በመታገል የባለድርሻ አካላት ሚና፣ ያሉት ተግዳሮቶችና መፍትሄዎች” የሚል የመወያያ ጽሁፍም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ምሁር ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ እንደሚቀርብ ተገልጿል።

እንደ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ፎረም መረጃ በየዓመቱ በጉቦና ስርቆት ብቻ የሚፈፀም ሙስና ከ3 ነጥብ 6 ትሪሊየን የአሜሪካን ዶላር በላይ የዓለም ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት እንደሚያደርስ መረጃዎች ያሳያሉ።

ከዚህ ውስጥ ከአፍሪካ ወደ 50 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ በህገ ወጥ መንገድ ሽሽት የሚፈፀም ሲሆን፥ በኢትዮጵያ ደግሞ ከግዢ እና ሌሎች አገልግሎት ዘርፎች ጋር ተያይዞ ከ35 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ በሙስና የሚባክን መሆኑ ተመላክቷል።

ይህ በሙስና የባከነ ሀብት ለመሰረተ ልማት አውታሮች፣ ለትምህርት ቤት ግንባታ፣ ለጤና ተቋማት፣ ለንፁህ መጠጥ ውሀ ፕሮጀክት፣ በጥቅሉ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ቢውል 43 በመቶ የሚሆኑ የዓለም ደሃ ህዝቦች ህይወት ይቀየር እንደነበር ጥናቶች ያመላክታሉ።

ምንጭ፦ኢዜአ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.