ጠ/ሚ ዐቢይ እና ሌተናል ጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን ዱከም የሚገኘውን ኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞንን ጎበኙ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሱዳን ሉአላዊ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን ዱከም የሚገኘውን ኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞንን ጎብኙ፡፡
በዚህ ጉብኝታቸውም የሰን ሽንግ ፋርማሲዩቲካል ፋብሪካ የሚያመርታቸውን የህክምና መድሀኒቶች እና የኦክስጅን የምርት ሂደት ተመልክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና ሌተናል ጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን ዛሬ ከሰዓት በኋላ ከጎበኙት ከኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን በተጨማሪ ቢሾፍቱ አቅራቢያ የሚገኝ ጆይ ቲክ የተባለ ዘመናዊ የግብርና ማዕከልንም ጎብኝተዋል።
ማዕከሉ በእስራኤላውያን ባለሀብቶች እየለማ የሚገኝ ሲሆን÷ አትክልትና ፍራፍሬ በአነስተኛ ቦታ በዘመናዊ መንገድበማምረት ለውጭ ገበያ የሚያቀርብ ነው።
ከዚያም ባለፈይህ ዘመናዊ የግብርና ማዕከል ፍራፍሬ ችግኞችን ለገበያ ሚያቀርብ መሆኑ ተገልጿል።
ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ዛሬ አዲስ አበባ የገቡት የሱዳን ሉአላዊ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በመሆን ቀደም ብለው የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጎብኝተዋል፡፡
ሌተናል ጄነራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን በኢትዮጵያ በሚኖራቸው የሁለት ቀናት ቆይታ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በአላዛር ታደለ
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።