ከ1 ሺህ ዓመት በላይ እድሜ ያለው የማያ ስልጣኔ ቤተ መንግሥት በቁፋሮ ተገኘ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 17፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የሜክሲኮ የስነ ምድር ተመራማሪዎች ከ1 ሺህ ዓመታት በፊት የተገነባ ቤተ መንግስት በቁፋሮ ማግኘታቸውን አስታወቁ።
ቤተ መንግስቱ በማያ የሥልጣኔ ዘመን አገልግሎት ይሰጥ የነበረ መሆኑንም ባለሙያዎቹ ገልጸዋል።
ስድስት ሜትር ቁመት፣ 55 ሜትር ርዝመት እና 15 ሜትር የሆነ ስፋት ያለው የቤተ መንግስት ፍርስራሽ በጥንታዊቷ የኩሉባ ከተማ ቤኩታን መንደር ነው በቁፋሮ የተገኘው።
ቤተ መንግስቱ ከ600 እስከ 1050 ባለው ዓመተ አለም ውስጥ ግልጋሎት ሳይሰጥ እንዳልቀረም ነው ባለሙያዎቹ የገለጹት።
ይህም በተለያዩ ሁለት የማያዎች የአስተዳደር ዘመናት ውስጥ ግልጋሎት የሰጠ እንደነበር ማሳያም ነው ብለዋል።
የስነ ምድር ተመራማሪ የሆኑት አልፍሬዶ ባሬራ የአሁኑ ስራ ጅምር መሆኑን ጠቅሰው መዋቅሮችን በደንብ ለይተው ማወቅ እንዳልጀመሩ አስረድተዋል።
በሜክሲኮ፣ ጓቴማላ፣ ቤሊዝ፣ ሆንዱራስና አካባቢው ተስፋፍቶ የነበረው የማያዎች ስልጣኔ ስፔን አካባቢውን ከመቆጣጠሯ በፊት መውደቁ ይነገራል።
ምንጭ፦ ቢቢሲ