የፀጥታ አካላትን የደንብ ልብስ በመልበስ ለስራ ጉዳይ በሚል ምክንያት ወደ መኖሪያ ቤቶች እና ተቋማት የሚሄዱ ግለሰቦችን ማንነት መለየት እንደሚገባ ተገለጸ
አዲስ አበባ ፣ጥቅምት 30 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፀጥታ አካላትን የደንብ ልብስ በመልበስ ለስራ ጉዳይ በሚል ምክንያት ወደተለያዩ መኖሪያ ቤቶች እና ተቋማት የሚሄዱ ግለሰቦችን ማንነት መለየት እና ማረጋገጥ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አሳሰበ፡፡
የህወሓት ህገወጥ ቡድን ተላላኪዎች የከተማዋን ሰላም ለማደፍረስ እንቅስቃሴ እያደረጉ እንደሚገኙ ከህዝብ በተገኘ ጥቆማ እና የፀጥታ አካላት ባደረጉት ክትትል ማረጋገጥ እንደተቻለ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
ኮሚሽኑ የህገወጥ ቡድኑ ተላላኪዎችን ተልዕኮ ለማክሸፍ እና በህግ ተጠያቂ ለማድረግ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ባከናወነው ተግባር በርካታ የጦር መሳሪያዎችን እና ለጥፋት መፈፀሚያ ሊውሉ የነበሩ የተለያዩ ንብረቶችን ከእነተጠርጣሪዎቹ ይዞ ምርመራ እያደረገ እንደሚገኝ መግለፁ ይታወሳል፡፡
ከተያዙት ንብረቶች መካከል የተለያዩ የፀጥታ አካላት የደንብ አልባሳት በግለሰብ መኖሪያ ቤት ውስጥ መገኘታቸውን ጠቅሷል።
ኮሚሽኑ አያይዞም የፀጥታ አካላቱን የደንብ ልብስ በመልበስ እና ተመሳስለው በመንቀሳቀስ የህወሓት ህገወጥ ቡድን ተላላኪዎች ጥቃት ሊፈፅሙ እንደሚችሉ በመገመት አስፈላጊው የክትትል ስራ እየተሰራ ነውም ብሏል፡፡
በዚህ በኩል የሚጋጥሙ ችግሮችን ለመከላከል የከተማችን ነዋሪዎች የፀጥታ አካላትን የደንብ ልብስ በመልበስ ለስራ ጉዳይ በሚል ምክንያት ወደተለያዩ መኖሪያ ቤቶች እና ተቋማት የሚሄዱ ግለሰቦችን ማንነት በትክክልም የፀጥታ አካል ስለመሆንና አለመሆናቸው የተቋማቸውን የስራ መታወቂያ ጠይቀው መለየት እና ማረጋገጥ እንዳለባቸው አሳስቧል፡፡
ፖሊስም ሆነ ሌሎች የፀጥታ አካላት የስራ መታወቂያ እንዲያሳዩ በተጠየቁ ጊዜ የማሳየት ግዴታ እንደተጣለባቸው ያስታወሰው ኮሚሽኑ ÷ መታወቂያቸውን ለማሳየት ፈቃደኛ ያልሆኑ ሲያጋጥሙ በመጠራጠር መረጃና ጥቆማውን በየአቅራቢያቸው ለሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎች በአካልም ሆነ በስልክ በማድረስ የከተማዋ ነዋሪዎች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ ማስተላለፉን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።