በሐዋሳ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች የህወሓት ጽንፈኛው ቡድን መከላከያ ሠራዊት ላይ ያደረሰው ጥቃት የሀገር ክህደት ነው ሲሉ አወገዙ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 3፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐዋሳ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች የህወሓት ጽንፈኛው ቡድን በመከላከያ ሠራዊት ላይ ያደረሰው ጥቃት አሳፋሪና ሀገርን የመካድ ነው ሲሉ አውግዘዋል።
በሐዋሳ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ዙሪያ ከከተማ አስተዳደሩና ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ተወያይተዋል።
የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ጸጋዬ ቱኬ÷ የህወሓት ቡድን ህዝብን መደበቂያ አድርጎ ጦርነት መክፈቱ አሳዛኝና አሳፋሪ መሆኑን የተናገሩ ሲሆን ህዝቡ ከምንግዜውም በላይ ለሰላም ሊተጋ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የሲዳማ ክልል ሠላምና ጸጥታ ቢሮ ኅላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዎስ በበኩላቸው ሴረኛው የህወሓት ቡድን ባልተጠበቀ ሁኔታ በመከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመው ግፍ አሳዛኝና ታሪክ የማይረሳው መሆኑን ገልጸው ቡድኑ የከፈተብንን ጦርነት ለመመከት ሁሉም በአንድነት መሰለፍ አለበት ብለዋል።
የሲዳማ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ በቀለ ቱንሲሳ በበኩላቸው ÷የህወሓት ቡድንና ተላላኪዎች የቀረበላቸውን የሰላም ጥሪ ወደ ጎን በማለት አጸያፊ ተግባር መፈጸማቸውን ተናግረዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም የህወሓት ጽንፈኛ ቡድን ከለውጡ ወዲህ በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በሚፈጥራቸው የጸጥታ ችግሮች የሰው ህይወትና ንብረት ላይ በደረሰው ኪሳራ ከፍተኛ ሃዘን እንደተሰማቸው ገልጸዋል።
ቡድኑ የተንኮል ሴራውን በማስፋት ለሃገሪቱ ደጀን በሆነው የሃገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ያደረሰው ጥቃት ኢትዮጵያዊ ከሆነ ወገን የማይጠበቅ አሳፋሪ ተግባር መሆኑንም ነው የተናገሩት ።
ከኢትዮጵያ ባለፈ ለውጪ ሠላም በማስከበር ኩራትና መከታ የሆነው የሃገር መከላከያ ሠራዊት በትግራይ ለህዝቡ እያከናወነ ያለው የልማት ተሳትፎ ሊያሸለመውና ሊያስወድሰው እንጂ ጥቃት ሊፈጸምበት አይገባም ነበር ብለዋል።
ለሀያ አመት የትግራይን ህዝብ ደህንነት ሲጠብቅ የኖረ መከላከያ ሠራዊት ላይ የተፈጸመው ጥቃት የሀገር ክህደት መሆኑን ጠቁመው÷ ለትግራይ ህዝብ በችግር ጊዜ የደረሰ መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት የፈጸመው የጥቂት ሆድ አደር ቡድኖች ስብስብ የትግራይን ህዝብ አይወክልምም ሲሉ ገልጸዋል።
አያይዘውም የህወሓት ቡድን ባለፉት ዓመታት በስማችን ሲነግድ በዚህም ለቡድኑ የሚላላክን ማንኛውም ሀይል በማጋለጥ ከመንግስት ጎን እንደሚቆሙ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።