Fana: At a Speed of Life!

ሕግን በማስከበር ዘመቻ የትግራይ ሕዝብ የመጀመሪያው ተጠቃሚ ይሆናል- ጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት

አዲስ አበባ፣ ህዳር 9፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር እና ሕገ ወጥ ወንጀለኞችን ለፍርድ ለማቅረብ ያለውን ቁርጠኝነት በድጋሜ ያረጋግጣል አለ የጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት።

ነገር ግን ይህ ሕግ የማስከበር እንቅስቃሴ በብሔር ወይም በሌላ ወገንተኝነት ላይ የተቃኘ ነው የሚለውን የተሳሳተ እሳቤ አጥብቆ ያወግዛል ብሏል ፅ/ቤቱ ዛሬ ባወጣው መግለጫ።

በአሁኑ ወቅት በትግራይ የሚካሄደው ሕግ የማስከበር ሥራ በዋነኝነት ኢትዮጵያን በማተራመስ ላይ በተሠማሩ ሥርዓት አልበኞች፣ በተንኮልና በሤራ በተሞሉ የሕወሐት ቡድን አባላት ላይ ያነጣጠረ ስለመሆኑ ማንም ሰው ጥርጣሬ ሊገባው አይገባም ብሏል በመግለጫው።

በትግራይ ክልል ሕዝብ ላይ ሳይቀር የከፋ በደል የሚፈጽመውን ይህን የሕወሐት ጁንታ የወንጀል ሰንሰለት ለማስቆም የፌዴራሉ መንግሥት ቆርጦ ተነሥቷል ሲልም ነው ያስታወቀው።

በዚህ ሕግ የማስከበር ዘመቻ የትግራይ ሕዝብ የመጀመሪያው ተጠቃሚ ይሆናል ያለው ፅ/ቤቱ፤ ለኢትዮጵያ ያለው ራእይ በብዝኃነት የሚኮሩ ብሔር ብሔረሰቦች በአንድነት የሚኖሩባት የበለጸገች ኢትዮጵያን ማየት መሆኑን አስታውቋል።

የትግራይ ሕዝብ ሕዝባችን ነው፤ በዚህ ሕዝባችን ላይ ምንም ዓይነት ክፉ ነገር እንዲደርስ አንፈልግም። ይሄንን የሚያደርጉትንም አንታገሥም ነው ያለው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.