የእንግሊዝ መንግስት በትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለውን የሕግ ማስከበር ዘመቻ አስፈላጊነት በሚገባ ተረድቷል – አምባሳደር ተፈሪ መለሰ
አዲስ አበባ ፣ ህዳር 12 ፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የእንግሊዝ መንግስት በትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለውን የሕግ ማስከበር ዘመቻ አስፈላጊነት በሚገባ መረዳቱን በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ ገለጹ።
የሕወሓት የጥፋት ቡድን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በትግራይ ክልል በሚገኘው የአገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ መንግስት በክልሉ የሕግ ማስከበር ዘመቻ እያካሄደ ይገኛል።
በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ ዘመቻውን በተመለከተ ለእንግሊዝ መንግስትና ለተፎካካሪ ፓርቲዎች የማስረዳት ስራ መከናወኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።
በተደረጉት ገለጻዎች የእንግሊዝ መንግስት የሕግ ማስከበር ዘመቻውን አስፈላጊነት በሚገባ መረዳቱን አመልክተዋል።
ዋናው የእነሱ ሀሳብ የሕግ ማስከበር እርምጃው በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅና የሰብአዊ ቀውስ እንዳይደርስ ነው ብለዋል።
በእንግሊዝ በተለያዩ ከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በአገር መከላከያ ሰራዊቱ ላይ የደረሰው ጥቃት እጅጉን እንዳስቆጣቸውም ነው አምባሳደር ተፈሪ የገለጹት።
ዳያስፖራው ኮሚቴዎችን በማቋቋም በትግራይ ክልል የሚካሄደውን የሕግ ማስከበር ዘመቻ በሚኖሩበት አካባቢ ላሉ የእንግሊዝ መንግስት ባለስልጣናት እያስረዱና እያስገነዘቡ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ኤምባሲው እቅድ በማውጣት በእንግሊዝ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን በመቅረብ ስለዘመቻው ማብራሪያ እየተሰጠ መሆኑን አምባሳደር ተፈሪ አመልክተዋል።
በሕግ ማስከበሩ ዙሪያ በየጊዜው የሚወጡ መረጃዎችን የማሳወቅ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ያስታወቁት አምባሳደሩ÷ “በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ “እኔም ለኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል ለአገር መከላከያ ሠራዊት ያዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ነገ ይካሄዳል” ብለዋል።
ለዚህም ስራ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች የተቋቋሙ ማህበራትና የሲቪክ ተቋማት የቅስቀሳ ስራ ሲያከናወኑ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
መርሃ ግብሩ በዙም መተግበሪያ አማካኝነት በበይነ መረብ እንደሚካሄድና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
በአጠቃላይ በለንደን የሚገኘው ኢትዮጵያ ኤምባሲ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሩን ጨምሮ 20 ሺህ ፓውንድ ለመከላከያ ሰራዊቱ ለማሰባሰብ እቅድ መያዙን ገልጸዋል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።