በደቡባዊ አፍሪካ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለህዳሴ ግድብ የቦንድ ግዢ ፈጸሙ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 14፣ 2013 (ኤፍቢሲ) በደቡብ አፍሪካ፣ ናሚቢያ፣ ቦትስዋና፣ ኢስዋቲኒ፣ ሌሴቶ፣ ሞዛምቢክ እና ማዳጋስካር የሚኖሩ ኢትዮጵውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለህዳሴ ግድብ 1 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር የቦንድ ግዢና ድጋፍ አበረከቱ፡፡
በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በደቡባዊ አፍሪካ የሚኖሩ ዜጎች ቀደም ሲል በሃገር ቤት የተከሰተውን የኮሮና ወረርሽኝ ለመከላከል ከ3 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር በላይ የገንዘብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሷል፡፡
በወረርሽኙ ምክንያት ችግር ላይ ለወደቁ በደቡባዊ አፍሪካ ለሚኖሩ ወገኖቻቸው ከ2 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውንም ገልጿል፡፡
በአጠቃላይ ከ6 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር በላይ የሆነ ድጋፍ በሀገር ቤት እና በደቡባዊ አፍሪካ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ማሰባሰብ ተችሏል፡፡
በተመሳሳይ በሃገር ሉዓላዊነት ላይ የተፈጸመውን ክህደትና ስርዓት አልበኝነት ለመቀልበስ ከፍተኛ ተጋድሎ እየፈጸመ ለሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት የሞራል፣ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲሰጥ ጥሪ መቅረቡንም ጠቅሷል፡፡
በዚህም ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ወደ 300 ሺህ ብር የሚጠጋ የገንዘብ ድጋፍ ለዚህ ተብሎ በኤምባሲው በተዘጋጀው እና ሃገር ቤት በተከፈተው የባንክ ሂሳቦች ገቢ አድርገዋል፡፡
የኤምባሲው ሰራተኞችም የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል፣ ለገበታ ለአገር ፕሮጀክት እንዲሁም ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የ3 ወር ደሞዝ መለገሳቸውንም አስረድተዋል፡፡
በደቡብ አፍሪካ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም ማህበረሰቡ ለወሳኝ ሃገራዊ ጥሪዎች እየሰጠ ላለው አስደናቂ ምላሽ ምስጋና ማቅረባቸው በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ገልጿል፡፡