Fana: At a Speed of Life!

በሞጣ ከተማ የእምነት ተቋማት ላይ ከደረሰው ጉዳት ጋር በተያያዘ የተለያዩ የሥራ ሃላፊዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ታህሳስ 21፣2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በሞጣ ከተማ አስተዳደር ታህሣሥ 10 ቀን 2012 ዓ.ም ከተፈጸመው የእምነት ተቋማት ቃጠሎ ጋር በተያያዘ የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ፡፡

በምሥራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ አስተዳደር በመስጅዶች፣ ቤተ ክርስቲያን እና ሱቆች ላይ የእሳት ቃጠሎ ተፈጽሟል፤ ንብረቶችም ተዘርፈዋል፡፡

በዚህ ሁኔታ በአግባቡ ኃላፊነታቸውን አልተወጡም ተብለው የተጠረጠሩ የተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በሕግ ቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የምሥራቅ ጎጃም ዞን ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር አያልነህ ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡

በዚህ መሰረትም  የሞጣ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ የፖሊስ ወንጀል መከላከል ኃላፊ ፣ የሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ እና የሚሊሻ ስምሪት ኃላፊ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉትም በወቅቱ ተገቢውን ሥምሪት ሰጥተው ተገቢውን መከላከል በማድረግ ሁኔታውን መቆጣጠር እየቻሉ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው ተጠርጥረው መሆኑን አብመድ ዘግቧል።

በታህሣሥ 10 ቀን 2012ዓ.ም ከሞጣ ሁኔታ ጋር በተያያዘ 33 ተጠርጣሪዎች በጊዜ ቀጠሮ ላይ ሲሆኑ፥ 35 ተጠርጣሪዎች ደግሞ ተይዘው ማጣራት እየተደረገባቸውና በዋስ የወጡ እንዳሉም ታውቋል።

በጣቢያ ቃላቸውን ገና ያልሰጡ ተጠርጣሪዎች እንዳሉም ተመላክቷል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.