የኦሮሚያ ክልል መንግስት ካቢኔ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 21፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ካቢኔ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።
ካቢኔው በዛሬው እለት ባካሄደው ስብሰባው የባሌ ዞን በሁለት ዞኖች እንደ አዲስ እንዲደራጅ እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ በማሳለፍ እንዲጸድቁ ለጨፌ ኦሮሚያ መርቷል።
በዚህም መሰረት የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ለካቢኔው ባቀረበው ጥናት በዞኑ ባለው የመሰረተ ልማት እና የቦታ መራራቅ ችግር የተነሳ አገልግሎት ፍጥነት ማቅረብ ባለመቻሉ ለረጅም ጊዜ የመልካም አስተዳደር ችግር ምንጭ ሆኖ መቆየቱን ጠቁሟል።
ካቢኔው ጥናቱን መነሻ በማድረግ ውይይት ካካሄደ በኋላ የባሌ ዞን የነበረው፤ ምስራቅ ባሌ ዞን እና ምእራብ ባሌ ዞን ሆኖ እንደ አዲስ እንዲደራጅ በሙሉ ድምጽ ወስኗል።
የምእራብ ባሌ ዞን ዋና ከተማ ሮቤ እንዲሁም የምስራቅ ባሌ ዞን ዋና ከተማ ደግሞ ጊኒር እንዲሆን የቀረበው ምክረ ሀሳብም በሙሉ ድምጽ መጽደቁ ነው የተገለፀው።
በሌላ በኩል የክልሉ መንግስት ካቢኔ ባካሄደው ስብሰባ የኦሮሚያ ክልል የማዕድን ልማት አስተዳደርን ለመወሰን የቀረበ ረቂቅ አዋጅ እና የኦሮሚያ መንገዶች ፈንድን ለማቋቋም የቀረቡ ረቂቅ አዋጆች ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ ለጨፌ ኦሮሚያ እንዲቀርብ ውሳኔ አሳልፏል።