Fana: At a Speed of Life!

በዚህ ሁሉ ግፍና መከራ እንዲንበረከክ የተሞከረው ሰራዊት ዛሬ መሰናክሉን አልፎ ዘመን የማይሽራቸውን ጀግኖች ሰጥቶናል

አዲስ አበባ፣ ህዳር 25፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በዚህ ሁሉ ግፍና መከራ እንዲንበረከክ የተሞከረው ሰራዊታችን ዛሬ ከዚያ ሁሉ መሰናክል አልፎ ዘመን የማይሽራቸውን ጀግኖች ሰጥቶናል።

አስር አለቃ ዋቆ አላኬ እና ምክትል አስር አለቃ ሃብታሙ ተስፋዬ የሰሜን ዕዝ 20ኛ ቃሉ ክፍለ ጦር አባላት ሲሆኑ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በጁንታው ስለተፈጸመው ክህደት ያላቸውን ትውስታ ለመከላከያ ሰራዊት ገጽ አጋርተዋል፡፡

ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ጁንታው ለዘመናት የጠነሰሰውን የክፋትና የሃገር ክህደት ሴራ በአስመሳይነት ባህሪው ለመሞሸር የክፍለ ጦሩን አመራሮች “ላበረከታችሁት አስተዋፅኦ ክብር ይገባችኋል” በማለት በሽልማት የተለበደ ሴራውን ለአመራሮቻችን እንካችሁ አለ በማለት ያስታውሳሉ፡፡

በዚህ ቅፅበት የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የሰራዊቱ አመራሮች ሰራዊቱ የያዘውን መሳሪያ ለንብረት ክፍል እንዲገባ ማድረጋቸውንም ይገልጻሉ።

ለሰራዊት አገልግሎት የሚሰጡ የውሃ ቦቴዎች፣ መገናኛ መንገዶች፣ የምግብና መጠጥ አቅርቦት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ሰራተኞችን በማፈን ሁሉም በጁንታው እንዲቋረጡ መደረጉን ያወሳሉ።

“የውትድርና ህይወት በባህሪው መተማመንን የሚያስቀድም ከአንተ ይልቅ እኔ ቀድሜ ልሙት የሚያስብል ወርቃማ እሴት ያለው በመሆኑ” የተሸረበውን ሴራ በውል የሚረዳ ይቅርና የሚጠራጠር እንኳን አልነበረም ይላሉ ጀግኖቹ።

በእምነት አብሯቸው የሚኖረውን ብቻ ሳይሆን ለደህንነታቸው ክብር ሲል ሳያመነታ ህይወቱን ለሰጣቸው ሰራዊት ከጀርባ ሆነው ተኮሱበት፣ ማምለጫ መንገድ እንዳይኖረው አድርገው ህይወቱን እንዲያጣ ማድረጋቸውንም ይናገራሉ።

ሰራዊቱ ለተከታታይ ሦስት ቀናት ካለምንም ምግብና ውሃ በርሃብ እንዲቀጣ ተደረገ የሚሉት ሁለቱ ጀግኖች፥ በረሃብ የተዳከመ ሰውነት ምንም ትጥቅ ያልያዘን ኃይል በፈለጉት የሞት ድግስ ውስጥ እንዲገባ በማድረግ ምሽቱን የተኩስ ናዳ እንዳወረዱበትም ያስረዳሉ፡፡

ይህ ሁሉ ግፍና መከራ ለምን? ስለሃገር በዱር በገድል የሚባክን፣ ከዕለት ጉርሱ ቀንሶ ለተቸገረ የሚረዳ፣ የራሱን ጉሮሮ አድርቆ የውሃ መጠጣት እርካታውን ውሰዱ ላለ ሰራዊት ፣ እንዴት ቢታሰብ ? በምን ህሊናስ ቢመዘን ለዚህ የጭካኔ ግፍ ሊበቃ ቻለ ? የሚለው ከጥቃት የተረፉ የሰራዊት አባላት የጋራ ጥያቄ ነው።

 

እርግጥ በሃገር ላይ የሚቃጡ መሰናክሎች ሁሉ እንደ ችግርነታቸው ሲታለፉ የራሳቸውን መልካም እድል ይዘው ይመጣሉ ፡፡

በዚህ ሁሉ ግፍና መከራ እንዲንበረከክ የተሞከረው ሰራዊታችን ግን ዛሬ ከዛ ሁሉ መሰናክል አልፎ ዘመን የማይሽራቸውን ጀግኖች ሰጥቶናል።

ከምንም በላይ ከእምዬ ኢትዮጵያ መቀነት ስር ሆኖ አንጀቷን የሚግጠውን የዘመናት ጥገኛ ትህነግ እስከ ወዲያኛው እንዲላቀቃት ምክንያት ሆኗልም።

በችግሮች ስንክሳር ተተብትበው ያልወደቁት የሠራዊቱ አባላት ራሳቸውን ከተደቀነባቸው እልህ አስጨራሽ መከራ አላቀውና እንደገና ተደራጅተው ጁንታውን ድል አድርገውታል።

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.