የመኾኒ ከተማ የሰላምና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መሻሻል እያሳየ ነው ተባለ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 9፣ 2013 (ኤፍቢሲ) የመኾኒ ከተማ ከንቲባ የነበሩት አቶ ጌታቸው አሸናፊ የመከላከያ ሰራዊቱ ወደ ከተማዋ ከገባ ጀምሮ የሰላምና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መሻሻል ማሳየቱን ተናገሩ፡፡
ከንቲባው የአካባቢው ወጣቶችና መላው የከተማዋ ነዋሪዎች የሰላም ጥበቃ ስራው ባለቤት በመሆን መከላከያ ሰራዊቱ የሚያከናውናቸውን ተግባራት እንዲደግፉ ጠይቀዋል።
“በተደጋጋሚ የምንሰማቸው ማስፈራሪያዎች ሰራዊቱን በጥርጣሬ እንድንመለከት በማድረጉ ራሴን ለማዳን ወደ ጫካ ገብቼ ነበር” ብለዋል፡፡
ሆኖም ለመከላለያ ሰራዊቱ እጃቸውን ከሰጡ በኋላ የተደረገላቸው እንክብካቤና ሰራዊቱ ለህዝብ ያለውን ፍቅር ሲሰሙት ከነበረው ጋር ፍፁም እንደማይገናኝም ገልጸዋል።
በተደጋጋሚ በተሰራጩ የሃሰት ፕሮፓጋንዳዎች ምክንያት በርካታ የከተማዋ አመራሮችና ወጣቶች ራሳቸውን ለማዳን ወደ ጫካ መውጣታቸውን የጠቆሙት ከንቲባው፥ መሬት ላይ ያለው እውነታ ግን የተለየ በመሆኑ በተለያየ ቦታ የሚገኙ የከተማዋ አመራሮች ወደ መደበኛ ስፍራቸው በመመለስ የሰላም ጥበቃ ስራው ባለቤት መሆን ይጠበቅባችዋል ሲሉም መክረዋል ።
የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት ስራ አስኪያጅ በመሆን ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ዳርጌ ግርማይ በበኩላቸው፣ የህግ ማስከበር ዘመቻውን ተከትሎ መኾኒ ከተማ የኢኮኖሚ ውድቀት፣ የመሰረተ ልማት ውድመት የደረሰባት መሆኑና ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የከተማዋ ህዝቦች ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ መግባታቸውን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት የተቋረጡ መሰረተ ልማቶች ወደ ስራ እንዲመለሱ በማድረግና የሚከሰቱ ችግሮችን በፍጥነት በመፍታት እውነተኛ የህዝብ ልጅ መሆኑን በተግባር በማሳየቱ መላው የከተማው ህዝብ ከመከላከያ ጎን በመሰለፍ የአካባቢውን ሰላም ለመጠበቅ ከምን ጊዜውም በላይ ዝግጁ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞን በምትገኘው የመኾኒ ከተማ በህግ ማስከበር ዘመቻው ተቋርጠው የነበሩ የመብራትና የስልክ አገልግሎቶች የተጀመሩ ሲሆን ህዝቡም ሙሉ በሙሉ ወደ መደበኛ የየዕለት እንቅስቃሴ መመለሱን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!