Fana: At a Speed of Life!

አምባሳደር ሳሚያ በዶሃ ከሱዳን አምባሳደር ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ መከሩ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 3 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ ) በኳታር የኢትዮጵያ አምባሳደር ሳሚያ ዘካሪያ በዶሃ ከሱዳን አምባሳደር አብደልራሂም አልሲዲግ ሞሃመድ ጋር በወቅታዊ ጉዳየች ዙሪያ መክረዋል።
ውይይቱ በህግ ማስከበር ዘመቻው፣ በወቅታዊ የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይ፣ በሕዳሴ ግድብ ላይ እየተደረገ ስላለው ድርድር እና የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ለማጠናከር ሚሲዮኖቹ በጋራ መስራት በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር።
በዚህ ወቅትም አምባሳደር ሳሚያ በህግ ማስከበር ዘመቻው እና አሁን ባለው ሁኔታ ላይ ለአምባሳደሩ ገለጻ አድርገውላቸዋል።
አምባሳደር አብዱልራሂም በበኩላቸው ÷የህግ ማስከበር ዘመቻው የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ መሆኑን በማስታወስ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን እና አገልግሎቶችን መልሶ በማቋቋሙ ሂደት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል።
የኢትዮ-ሱዳን ድንበርን በተመለከተም አምባሳደር ሳሚያ ጉዳዩ ለረጅም ዓመታት መፍትሔ ሳይበጅለት የዘለቀ እና የራሱ ኮሚቴዎች ተዋቅረውለት በውይይት ላይ የሚገኝ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በመሆኑም አሁንም በውይይት እና በሚመለከታቸው ኮሚቴዎች በኩል እልባት እስከሚሰጠው ከሰሞኑ ክስተት በፊት የነበረው ነባራዊ ሁኔታ እንዲቀጥል መስራት ያስፈልጋልም ብለዋል።
ጉዳዩ ለረጅም ዓመታት የዘለቀ እና በሰላማዊ መንገድ መፍትሔ ሊበጅለት የሚችል እንደሆነ ገልጸዋል።
የሕዳሴ ግድብን እና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተም አምባሳደሮቹ ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ የመፍትሔ ሐሳቦች በሚለው መርህ መሰረት የሌላ ወገን ጣልቃ ገብነት ሳያስፈልግ በውይይት እና ድርድር ጥቅምን ማስጠበቅ ይገባል የሚል የጋራ ሐሳብ አንጸባርቀዋል።
ሁለቱ ሚሲዮኖች የሕዝብ ለሕዝብ መድረኮችን በመፍጠር፣ የባህል፣ የቱሪዝም፣ የኢንቨስትመንት እና ሌሎች አውደ ርዕዮችን በጋራ በማዘጋጀት ግንኙነቱን የበለጠ ለማጠናከር መስማማታቸውን ዶሃ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.