በመዲናዋ በትምህርት ቤቶች ዙሪያ ለሱስ የሚያጋልጡ የንግድ ተቋማት ተበራክተዋል
አዲስ አበባ ፣ ጥር 1 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ በትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማሩን ሂደት የሚያውኩና ተማሪዎችን ለሱስ የሚያጋልጡ የንግድ ተቋማት መበራከታቸውን ነዋሪዎች ገለጹ።
አስተያየታቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የሰጡ ነዋሪዎች እንደሚሉት፥ ተማሪዎች ደንበኛ እንዲሆኑ ትኩረት ያደረጉ የንግድ ተቋማት በትምህርት ቤቶች አካባቢ ተበራክተዋል።
በተለይም አሁን አሁን ተቋማቱ በመጠን እና በአይነት ጨምረው ዘርፈ ብዙ እየሆኑ መምጣታቸውንም ያነሳሉ።
ይህም በነገ ሃገር ተረካቢ ትውልድ ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድር በመሆኑ መፍትሄ ሊበጅለት እንደሚገባ አንስተዋል።
ችግሩ መኖሩን የሚያምነው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቢሮ፥ የንግድ ተቋማት በትምህርት ቤቶች አካባቢ መበራከት ለመማር ማስተማሩ ሂደት እንቅፋት መፍጠሩን ይገልጻል።
የንግድ ተቋማቱ ፍቃዳቸውና ስራቸው የተለያየ መሆኑን የጠቀሰው ቢሮው ችግሩ ተለዋዋጭ እና ዓይነቱን እየቀያየረ መምጣቱንም ገልጿል።
ፈቃድ ሰጭ የሆነው የአዲስ አበባ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ደግሞ ፍቃድ በሚሰጥበት ጊዜ ፍቃድ ጠያቂው የሚሰራበትን ቦታ አካባቢው ድረስ ሄዶ ማየት የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ እንደሌለው ያስረዳል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ችግሩ መኖሩን ጠቅሶ፥ ችግሩን ለመቅረፍ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልጿል።
ከዚህ ባለፈ ግን ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ በትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚከፈቱ የንግድ ተቋማት፥ ከትምህርት ቤቶች ዙሪያ 200 ሜትር እንዲርቁ የሚያስገደድ ረቂቅ ደንብ ማዘጋጀቱንም አስታውቋል።
ረቂቅ ደንቡን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት እንዲጸድቅለት ማቅረቡንም ነው የገለፀው።
ከሚወጣው ደንብ በተጨማሪም ወላጆች፣ መምህራን፣ ተማሪዎችና ማህበረሰቡ የሚያደርጉትን ተሳትፎ ሊያጠናክሩ ይገባልም ብሏል።
በሲሳይ ጌትነት