Fana: At a Speed of Life!

የሀረር ሰዎች ለሰዎች የአግሮ ቴክኒክና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ 183 ሰልጣኞችን አስመረቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የሀረር ሰዎች ለሰዎች የአግሮ ቴክኒክና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ በተለያዩ መስኮች ያሰለጠናቸውን 183 ሰልጣኞችን በዲግሪ አስመረቀ።

በዶ/ር ካርል ሄንዝ በም የተመሰረተውና በተለያዩ የአግሮ ቴክኒክና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ተማሪዎችን ተቀብሎ ከ1984 ዓ.ም የሚያሰለጥነው የሠዎች ለሠዎች ኮሌጅ በግብርና፣በቴክኖሎጂና በማኑፋክቸሪንግ የትምህርት ዘርፎች እስከ አራት ዓመታት ያሰለጠናቸውን ተማሪዎችን ነው ያስመረቀው።

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተው ለተመራቂዎች ዲግሪና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ሽልማት የሰጡት የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ባስተላለፉት መልዕክት የሠዎች ለሠዎች ድርጅት ከምስረታው ጀምሮ ከእለት እርዳታና ድጋፍ ባሻገር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በመደገፍና በማፋጠን ያበረከተውና እያበረከተ ያላው ድርሻ አቻ አይገኝለትም ካሉ በኋላ ድርጅቱ በየጊዜው አሳታፊነቱን፣ደረጃውንና የትምህርትና ስልጠና ጥራቱን እያሳደገ መጥቶ በእውቀት፣ በክህሎትና በስነ ምግባር የታነፀ የሠው ኃይል በማፍራት ረገድ የሀረር አግሮ ቴክኒካል ኮሌጅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱን አስታውቀዋል።

አቶ ኦርዲን አያይዘውም ተመራቂዎች በኮሌጅ ቆይታቸው የቀሰሙትን እውቀትና ክህሎት በመጠቀም ቴክኖሎጂዎችን በመለየት፣በመምረጥና በመቅዳት ብሎም በተግባር በመፈተሽ ወደ ተጠቃሚዎች በማሸጋገር የሃሪቱን ብልፅግና ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስረ መጣር እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል።

የሀረር የሠዎች ለሠዎች የአግሮ ቴክኒክና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አበበ ፋንታ በበኩላቸው ኮሌጁ በኮቪድ ሳቢያ ሐምሌ ላይ መመረቅ የነበረባቸውን ተማሪዎቹን በግብርና ዘርፍ በእንስሳትና እፅዋት ልማት፣ በቴክኖሎጂ ዘርፍ በአውቶሞቲቭ፣በኤሌክትሪክና ኤሌክትሮኒክስ እንዲሁም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ያሰለጠናቸው መሆኑን ገልፀው ኮሌጁ በዲግሪ ደረጃ የሚሰጣቸው ስልጠናዎች የሃገሪቱን ችግር የሚፈቱና ጉድለት የሚሞሉና ድግግሞሽን የሚያስወግዱ እንዲሆኑ ጥናት ማድረጉን ገልፀዋል።

ተመራቂ ተማሪዎችም በተማሩበት መስክ በመሰማራት ችግር ፈቺ የሆኑ ስራዎችን በመስራት ሃገሪቱ ከግብርና መርህ ወደ ኢንደስትሪ ለመሸጋገር በምታደረገው ጥረት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማበርከት መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።

የሠዎች ለሠዎች የአግሮ ቴክኒካና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ካስመረቃቸው 183 ሰልጣኞች መካከል 40ዎቹ ሴቶች ሲሆኑ የአሁኖቹን ተመራቂዎች ሳይጨምርይ ከ1984 ዓ/ም ጀምሮ ከሦስት ሺህ አንድ መቶ በላይ ሰልጣኞችን በዲፕሎማና በዲግሪ መርሃ ግብሮች አሰልጥኖ በማስመረቅ ወደ ስራ ማሰማራቱን በዚሁ ወቅት ተመላክቷል።

በተሾመ ኃይሉ

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.