በደቡብ ክልል በሚቀጥሉት ሶስት ቀናት የበረሃ አንበጣ ሊከሰት እንደሚችል ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በደቡብ ክልል በሚቀጥሉት ሶስት ቀናት የበረሃ አንበጣ ሊከሰት እንደሚችል የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።
የአንበጣ መንጋዉ በአጎራባቹ ኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ተልተሌ ወረዳ መታየቱን ተከትሎ የቅደመ ጥንቃቄ እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል።
የደቡብ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ዳንኤል ዳምጠዉ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፥ የአንበጣ መንጋዉ በክልሉ በኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ፀማይ፣ቡርጂና በኦሮሚያ አጎራባች ወረዳዎችም ላይ ሊከሰት ይችላል ብለዋል።
አንበጣውን ለመከላከልም ቢሮዉ ከፌዴራል መንግስት ጋር በመሆን የኬሚካል ርጭት ለማድራግ ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን በመግለጫቸዉ ጠቅሰዋል።
የአንበጣ መንጋው የሚመጣ ከሆነ ህብረተሰቡ በባህላዊ መንገድ ለመከላከል መዘጋጀት እንዳለበትም ጥሪ አቅረበዋል።
በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን 11 ወረዳዎች የአምበጣ መንጋ መከሰቱ ይታወቃል።
በዞኑ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል ከፌዴራል መንግስት በተገኘ ድጋፍ በአውሮፕላን የኬሚካል ርጭት እየተደረገ መሆኑን ዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ዳውድ አብዱሪ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።
በጥላሁን ይልማ