Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ከደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ራማፎሳ ጋር ተወያዩ

አበባ፣ ጥር 3፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በደቡብ አፍሪካ ይፋዊ የስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ጋር ተወያዩ።

መሪዎቹ በፕሪቶሪያ ባደረጉት ውይይትም በተለያዩ የሁለትዮሽ እና አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

ሁለቱ መሪዎች ከተወያዩ በኋላ ሀገራቱ የተለያዩ ስምምነቶችን እና የመግባቢያ ሰነዶችንም ተፈራርመዋል።

በተለይም በጤና እና በቱሪዝም መስክ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

በመቀጠልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ጋር በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በዚህም ወቅት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለልዑካቸው ለተደረገው ደማቅ አቀባበል ምስጋና አቅርበዋል።

በደቡብ አፍሪካ ኢትዮጵያውያን እንደ ሀገራቸው እየኖሩ መሆናቸውን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በጉብኝታቸው ወቅት በሀገሪቱ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ አንስተው መምከራቸውን ተናግረዋል።

በተለይም ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ ፕሬዚዳንቱ ችግሩን ለመፍታት መስማማታቸውን ነው ያነሱት።

ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ጉዳይን በፍጥነት ለመፍታት የሀገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የሚገኙባቸው የጋራ ኮሚቴ ተቀቁሞ ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲመቻች መስማማታቸውን አስታውቀዋል።

በርካታ ኢትዮጵያውያን በደቡብ አፍሪካ በተለያዩ የስራ መስኮች ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን ማፍሰሳቸውን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ደቡብ አፍሪካውያንም ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በተለያዩ መስኮች እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በተለይም ለሀገሪቱ የግል ዘርፍ ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ መኖሩን በማንሳት ነው የጋበዙት።

በአጠቃላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የደቡብ አፍሪካ ጉብኝታቸው የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት አጠናክሮ ወደፊት ለማስቀጠል እድል መፍጠሩን ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንት ራማፎሳ በበኩላቸው ውይይታቸው የሀገራቱን ግንኙነት ስትራቴጂካዊ ለማድረግ እድል የፈጠረ መሆኑን ነው ያነሱት።

በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የሚደርስባቸውን ጥቃት ለመከላከል የችግሩን ስር በማጥናት መፍትሄ ለመስጠት መንግስታቸው እየሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

 

በአልአዛር ታደለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.