መገናኛ ብዙሃን ምርጫ ነክ መረጃዎችን ሚዛናዊ በሆነ መልኩ መዘገብ እንዳለባቸው ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) መገናኛ ብዙሃን የፖለቲካ ፓርቲዎች ለህዝቡ የሚያቀርቧቸውን ፖሊሲዎች እና ፕሮግራሞች ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ማስተላለፍ እንደሚገባቸው የዘርፉ ምሁራን ገልጸዋል።
ከፋና ብሮድካስቲን ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የዘርፉ ምሁራን፥ ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ካካሄደቻቸው ምርጫዎች ተሞክሮ በመውሰድ በመጪው ምርጫ የሚሳተፉ ፓርቲዎች የያዙትን አጀንዳ መራጩ ጠንቅቆ የሚያውቅበት ሜዳን የማዘጋጀት ሃላፊነት እንዳለባቸው አንስተዋል።
በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ኮሙዩኒኬሽን ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ጀማል መሃመድ፥ መገናኛ ብዙሃን በሀገራዊ ምርጫው የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ፖሊሲ እና ፕሮግራም ለህዝቡ ተደራሽ በማድረግ በኩል ከፍተኛ ሚና መጫወት እንዳለባቸው አብራርተዋል።
መረጃዎችን በማሰራጨት ረገደም መገናኛ ብዙሃን ለሁሉም ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ፍትሃዊ እና ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ሽፋን መስጠት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ትምህርት ክፍል ሃላፊ ዶክተር ጌታቸው ጥላሁን በበኩላቸው፥ መገናኛ ብዙሃን በቅድመ ምርጫም ሆነ በምርጫ ወቅት ትክክለኛ ዘገባን ከማሰራጨት ባሻገር ለፓርቲዎች የሚሰጡት ሽፋን ገለልተኛ ሊሆን እንደሚገባ አንስተዋል።
በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ሳይንስ መምህርሩ አቶ ንጋቱ አበበ፥ መገናኛ ብዙሃን የፖለቲካ ፓርቲዎችን ፖሊሲና ፕሮግራም መራጩ ማህበረሰብ በትክክል እንዲረዳ የማድረግ ሃላፊነት ያለባቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ይህንን ሃሳብ በተገቢው መልኩ ገቢራዊ ለማድረግም መገናኛ ብዙሃን ከወገንተኝነት በጸዳ መልኩ ስራቸውን ማከናወን አለባቸው ነው ያሉት።
የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ መጪው ምርጫ የሚካሄድበትን ቀን ይፋ ለማድረግ መዘግየቱን የተናገሩት ምሁራኑ፥ መገናኛ ብዙሃን የፖለቲካ ፓርቲዎችን የመከራከሪያ ምህዳር ከመፍጠር አኳየ ከወዲሁ ሊዘጋጁ እንደሚገባ ገልጸዋል።
በሃይለኢየሱስ መኮንን