በኦሮሚያ ክልል ግንባታቸው የዘገዩ ስድስት ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ ፣ ጥር 8 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ግንባታቸው የዘገዩ ስድስት የመንገድ ፕሮጀክቶችን ከ556 ሚሊየን ብር በላይ ተጨማሪ በጀት በመመደብ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ።
በምክትል ርዕስ መስተዳድር ማዕረግ የግብርና ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ የተመራው ልዑክ በምዕራብ ኦሮሚያ በሚገኙ አራት ዞኖች በስፍራው የክትትልና ድጋፍ ጉብኝት አድርጓል።
በተጨማሪም የክልሉ መንግስት በክልሉ የመንገድ ባለስልጣን መስሪያ ቤት ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎችን በማዋቀር ለሶስት ወራት ጥናት ሲያደርግ መቆየቱ ተገልጿል።
ግንባታቸውን ለማጠናቀቅ የክልሉ መንግስት በልዩ ሁኔታ ከ556 ሚሊየን ብር ተጨማሪ በጀት በመፍቀድ የመንገዶቹን ግንባታ በተያዘው ዓመት ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው።
በምክትል ርዕስ መስተዳድር ማዕረግ የግብርና ክላስተር አስተባባሪው ዶክተር ግርማ አመንቴ ከወሰን ማስከበር፣ ከግንባታ ማሽነሪዎች አቅርቦትና በቅንጅታዊ የአሰራር ክፍተት የሚስተዋሉ ችግሮችን በማረም ተቋራጮችና አማካሪዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ የመንገዶቹን ግንባታ እንዲያጠናቅቁ አሳስበዋል።
የክልሉ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ደጀኔ ፍቃዱ በበኩላቸው ለመልካም አስተዳደር ችግር መንስኤ የሆኑና የክልሉን መንግስት ለተጨማሪ ወጪ የዳረጉ መንገዶችን በተቀመጠው የጊዜ ገደብ በማያጠናቅቁ ተቋራጮች ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።
ፕሮጀክቶቹ በጅማ፣ ቡኖ በደሌ፣ ኢሉ አባቦራ እና ምዕራብ ሸዋ ዞኖች የተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ ሲሆን፥ ግንባታቸው ተጀምሮ እስከ 6 ዓመት የዘገዩ ናቸው።
በበላይ ተስፋዬ