የአዲስ አበባ ፖሊስ 500 መደበኛ የፖሊስ አባላትን አስመረቀ
አዲስ አበባ ፣ ጥር 9፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ፖሊስ ለ7 ወራት ሲያሰለጥናቸው የነበሩትን 500 መደበኛ የፖሊስ አባላትን አስመረቀ፡፡
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል እንዳሻው ጣሰው፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ፣ ሌሎች ኮሚሽነሮች ፣ እና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በምረቃ ስነ -ስርዓቱ ላይ ተገኝተዋል፡፡
ኮሚሽነር ጄኔራል እንዳሻው ጣሰው ባደረጉት ንግግር ተመራቂ የፖሊስ አባላት በስልጠና ወቅት ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት በመጠቀም ህዝብ የጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃትና በታማኝት መወጣት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ፖሊሳዊ ሙያ እስከ ህይወት መስዋዕትነት የሚጠይቅ መሆኑን በመገንዘብ ሀገራዊ ሀላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባም ነው ኮሚሽነር ጄኔራሉ ያሳሰቡት፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በበኩላቸው የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ትልቅ ኃላፊነት ካለባቸው ተቋማት አንዱ ፖሊስ ኮሚሽኑ መሆኑን በመግለፅ ተቋሙ በሀገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ላይ ልዩ ልዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የፖሊስ አካዳሚ ዳይሬክተር ረዳት ኮሚሽነር መኮንን አሻግሬ የከተማዋን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ባህሪዋን የሚመጥን የስልጠና ተቋም መፍጠር ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
ተመራቂዎችም ህዝብና መንግስት የጣለባቸውን ኃላፊነት በታማኝትና በቁርጠኝነት ሊወጡ ዝግጁ መሆናቸውን መግለፃቸውን ከአዲስ አበባ ፓሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡