የሰላም ሚኒስትሯ ከተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ ፣ ጥር 11 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል ከተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የሃገር ውስጥ ሚኒስትር ሌተናል ጄነራል ሼክ ሳይፍ ቢን ዛይድ አል ናህያን ጋር ተወያዩ።
በውይይታቸው ወቅት ሁለቱ ሃገራት ባላቸው የትብብር መስኮች ዙሪያ መክረዋል።
በተለይም በማህበረሰብ አቀፍ ፖሊሲ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ምክክር አድርገዋል።
በምክክራቸው ላይ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀኔራል እንዳሻው ጣሰውን ጨምሮ ሌሎች የፌደራል ፖሊስ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
በተያያዘም የሰላም ሚኒስትሯ ከአቡ ዳቢ ለልማት ፈንድ ጄኔራል ዳይሬክተር ሞሃመድ ሳይፍ አል ሱዌይዲ ጋር ውይይት አድርገዋል።
በውይይታቸው ወቅትም በኢትዮጵያ የልማት ፕሮጀክቶችን መደገፍ እና የኢንቨስትመንት አማራጮችን መለየት በሚቻልበት አግባብ ላይ መክረዋል።
የሰላም ሚኒስትሯ በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር የልማት ፈንዱ እና የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬትስ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ልማት ለሚያደርጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
አያይዘውም የልማት ፈንዱ በተለያዩ የዓለም ሃገራት ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊ ዘርፎች ለሚያደርገው ድጋፍ ያላቸውን አድናቆትም ገልጸዋል።
ጄኔራል ዳይሬክተሩ በበኩላቸው ፈንዱ በታዳጊ ሃገራት በተለይም በአፍሪካ የሚያደርገውን የልማት እንቅስቃሴ የማስፋት ፍላጎት እንዳለው ገልጸዋል።
አያይዘውም የልማት ፈንዱ በአፍሪካ የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች የመንግስታቱን ድርጅት ዘላቂ የልማት ግቦች ለማሳካት የሚደረገውን ጥረት በሚደግፍ መልኩ ውጤት እያመጡ መሆኑን አስረድተዋል።
ጉብኝቱም በኢትዮጵያ መንግስትና በልማት ፈንዱ መካከል የልማት ፕሮጀክቶችን መደገፍና ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት በሚቻልበት አግባብ ላይ ተባብረው መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ለመምከር የሚያስችል እድል ይፈጥራልም ነው ያሉት።
የአቡ ዳቢ ለልማት ፈንድ ከፈረንጆቹ 2012 ጀምሮ በኢትዮጵያ ከ32 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር በላይ ለሚያወጡ ፕሮጀክቶች ድጋፍ አድርጓል።
መረጃው የኢሚሬትስ የዜና አገልግሎት ነው