ሁሉንም የካንሰር አይነቶች ማከም ያስችላል የተባለው አዲስ ግኝት…
አዲስ አበባ፣ ጥር 13 ፣ 2012(ኤፍ ቢ ሲ) አዲስ የተገኘው የሰውነትን በሽታ የመከላከል ስርዓት ሁሉንም የካንሰር አይነቶች ለማከም እንደሚያስችል አዲስ ጥናት አመላከተ።
በሰዎች ደም ውስጥ የሚገኝ “ቲ” የተሰኘው ነጭ የደም ህዋስ በተፈጥሮ ካንሰር በሰውነት ውስጥ እንዳይኖር የማድረግ አቅም እንዳለው በጥናቱ ተመላክቷል።
ህዋሱ በሰውነት ውስጥ የካንሰር ስጋት መኖሩን በመፈተሽ እንዲሁም በማጥቃት ሁሉንም የካንሰር አይነቶች ይከላከላል ነው የተባለው።
በካርዲፍ የህክምና ቡድን አባላት ይፋ የተደረገው ይህ አዲስ ግኝት በሳንባ፣ ቆዳ፣ ደም፣ አንጀት፣ ጡት፣ አጥንት፣ የማህጸን በር እና የኩላሊት ካንሰርን አምጭ ተህዋስያንን ማሰስ እና መግደል እንደሚችል ተነግሯል፡፡
በዚህም በካንሰር በሽታ ከተጠቃ ሰው የደም ናሙና በመውሰድ እና ህዋሱን በዘረመል የማራቢያ ዘዴ አስተካክሎ ወደ ህመምተኛው በመመለስ ሁሉንም የካንሰር አይነቶች መከላከል እንደሚቻል ተጠቁሟል።
ግኝቱ እስካሁን በእንስሳት ላይ ብቻ የተሞከረ ሲሆን፥ ሰዎች ላይ ከመሞከሩ በፊት የደህንነት ማረጋገጫ እንደሚያስፈልገው ተጠቁሟል።
አዲሱ ግኝት የካንሰር በሽታን በመከላከል እንዲሁም ተመራማሪዎች ለካንሰር በሽታ አዲስ መድሃኒት እንዲያገኙ የሚያስችል ፍንጭ በመስጠት ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ታምኖበታል።
ምንጭ፡- ቢቢሲ