Fana: At a Speed of Life!

ህወሓት ህልውናውን ለማስቀጠል ግጭትን እንደመሳሪያ የሚጠቀም አሸባሪ ድርጅት ነው – ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 7 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ህወሓት ህልውናውን ለማስቀጠል ግጭትን እንደመሳሪያ የሚጠቀም አሸባሪ ድርጅት መሆኑን የመከላከያ ሰራዊት የግንባታ ስራዎች ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ ገለጹ፡፡

ሌተናል ጀኔራል ባጫ ዛሬ በሰጡት መግለጫ መንግስት በትግራይ ክልል የተናጥል የተኩስ አቁም ተግባራዊ ማድረጉን አስታውሰው፥ ከዚህ ጋር ተያይዞም ሰራዊቱን ከትግራይ ክልል ማስወጣቱን አውስተዋል፡፡

ይሁን እንጅ አሸባሪው ህወሓትና የጁንታው ውጫዊ ሃይል የመንግስትን የተናጥል የተኩስ አቁም ውሳኔ ወደጎን በመተውና እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ትንኮሳ መፈጸማቸውን ገልጸዋል፡፡

መከላከያ ሰራዊት በራያ ግንባር ከወጣ በኋላም መቋቋም ሳያደርግ ጁንታው አጋጣሚውን በመጠቀም መከላከያን አጥቅቶ ለመደምሰስ ሙከራ አድርጓልም ነው ያሉት፡፡

ጁንታው በመንግስት የተወሰነውን የተናጥል የተኩስ አቁም ስምምነቱን ለመቀበል ባህሪው እንደማይፈቅድለትም ተናግረዋል፡፡

የተኩስ አቁም ስምምነቱንም ጁንታው ከትግራይ ህዝብ የሚቀርብለትን ጥያቄ መመለስ ስለማይችል እና ከህዝብ የሚነጥለው ጉዳይ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም አሁን ላይ ትንኮሳውን ቀጥሏል ነው ያሉት ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ፡፡

ህዝቡም ወታደራዊ ስራ በወታደራዊ ስርአት እንጅ በአክቲቪስቶች የሚከናወን ስራ አለመሆኑን ሊረዳ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በዚህም መቸ እና የት ቦታ ማጥቃት እንዳለበት ተወስኖ እየተሰራበት ያለ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል፡፡

“ጉዳዩ ውጊያ ነው፤ ውጊያ ደግሞ ኢትዮጵያን እንደ ሃገር የማስቀጠልና የወያኔን ሃገርን የመበተን እቅድ የማይሳካ መሆኑን ማረጋገጥ ነው” ብለዋል፡፡

“ህዝቡም ወያኔ በሚፈጥረው ፕሮፓጋንዳ ሳይደናገጥ ለጉዳዩ ጆሮ ሊሰጠው አይገባምም” ነው ያሉት፡፡

መከላከያ ሰራዊት እየተዋጋ ያለው ለኢትዮጵያ ድንበር ነው ያሉት ሌተናል ጀኔራል ባጫ÷ ድንበሩም መረብ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ሰራዊቱም የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ እና የግዛት አንድነቷን ለማረጋገጥ ከመቼውም ጊዜ በላይ መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

ስለሆነም ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደ በፊቱ ሁሉ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመቆም አስፈላጊውን ድጋፍ አንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.