በእስራኤል የኢትዮጵያን ቡና ለማስተዋወቅ የተዘጋጀ አውደ ርዕይ እና የምክክር መድረክ ተካሄደ
አዲስ አበባ ፣ ጥር 18 ፣ 2012 (ኤፍቢሲ) በእስራኤል የኢትዮጵያን ቡና ለማስተዋወቅ የተዘጋጀ አውደ ርዕይ እና የምክክር መድረክ ተካሄደ።
በእስራኤል የኢፌዴሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ረታ ዓለሙ ሃገራቱ በንግዱ ዘርፍ ያላቸውን ትስስር ማጠናከር አለባቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ቡና በእስራኤል እንዲተዋወቅ እና ሰፊ ገበያ እንዲያገኝ ኤምባሲው ከእስራኤል የንግዱ ማህበረሰብ ጋር በትብብር ለመስራት ያለውን ዝግጁነት ገልጿል።
በእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የምስራቅና የደቡብ አፍሪካ ክፍል ዳይሬክተር አምባሳደር ያሄል ቪላን፥ ሃገራቱ ካላቸው ወዳጅነት አንጻር የንግድ ልውውጡን ለማጠናከር በጋራ መስራት እንደሚቻል ገልፀዋል።
የእስራኤል የንግዱ ዘርፍም የኢትዮጵያን ቡና በማስመጣትና የንግድ ግንኙነቱን በማጠናከር ረገድ ወሳኝ ሚና እንዲጫወት መንግሥት ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት።
የእስራኤል አፍሪካ ንግድ ምክር ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር አያላ ዊትነር በሁለቱ ሀገራት የንግድ ማህበረሰብ መካከል ትስስር በመፍጠር የኢትዮጵያን ቡና ወደ እስራኤል ገበያ ማቅረብ እንደሚቻል ተናግረዋል።
በመድረኩ ላይ እስራኤል ከኢትዮጵያ የምታስመጣውን ቡና ለማሳደግ የሁለቱ ሃገራት ቡና ነጋዴዎች ተቀራርበው መሥራት እንዳለባቸው ተነስቷል።
መረጃው በእስራኤል የኢትዮጵያ ኤምባሲ ነው፤