Fana: At a Speed of Life!

ዓለም አቀፍ እና የግብጽ ሚዲያዎች በህዳሴው ግድብ 2ኛ ዙር የውሃ ሙሌት ዙሪያ ምን አሉ ?

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 13 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የግብጽ አህራም ኦን ላይን፥ ኢትዮጵያ ግድቡን ሞልቻለሁ ብላለች የሚል ርዕስ በመሰጠት ከሙሌቱ ጋር ተያይዞ የተለያዩ ሃሳቦችን አንስቷል፡፡

የውሃ ሙሌቱ የታችኞቹ የተፋሰስ ሀገራት ማለትም ግብጽ እና ሱዳን ሳይስማሙ የተከናወነ ነው ይላል አህራም ኦንላይን፡፡

የግድቡን ሙሌት ለማጣጣል ጥረት ያደረገው ዘገባው፥ ካይሮ እና ካርቱም አይናቸውን ሳይነቅሉ የግድቡን ደህንነት በአሳሪ ህግ ዋስትና እንዲኖረው እና ግድቡ በግብጽ እና በሱዳን ህዝቦች ላይ ጉልህ ጉዳት አለማድረሱን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል የሚል ምክረ ሀሳብ የመለገስ አዛማሚያም አሳይቷል፡፡

ቢቢሲ ደግሞ ኢትዮጵያ  ውዝግቡ በበረታበት ወቅት ግድቡን በመሙላት ኢላማዋን አሳክታለች የሚል ዘገባ ይዞ ወጥቷል፡፡

የህዳሴውን ግድብ በመሙላት የሁለተኛውን ዓመት እቅድ በማሳካት በወራት ውስጥ ኤሌክትሪክ እንደሚያመነጭ የኢትዮጵያ መንግስት አስታውቋልም ብሏል፡፡

“አከራካሪው የቢሊየን ዶላሮች ግድብ በግብጽ እና በሱዳን ላይ ስጋት ፈጥሯል” በሚል አተታውን የቀጠለው የቢቢሲ ዘገባ ፥ የግብጽ ባለስልጣናት ትልቁ ጉዳያቸው አድርገውታልም ብሏል በዘገባው፡፡

የኢትዮጵያ ውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ  አሁን ላይ በቂ ውሃ በመኖሩ ሁለት ተርባይኖች መስራት ጀምረዋል ማለታቸውን  በዘገባው አካቷል፡፡

አልጀዚራ በበኩሉ የህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ሙሌት መጠናቀቁን ኢትዮጵያ አስታወቀች በሚል ርዕስ ዘገባ ሰርቷል፡፡

ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ  በትዊተር ገጻቸው ያሰፈሩት ጽሁፍ  በመጥቀስ እንደዘገበው፣ የሁለተኛ ዙር ሙሌት መጠናቀቁና እና ውሃ በግድቡ አናት ላይ እየፈሰሰ ነው ብሏል።

ፍራንስ 24 ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው ዘገባ ደግሞ ኢትዮጵያ አከራካሪውን ሜጋ ግድብ በመሙላት የሁለተኛውን ዓመት ግቧን አሳክታለች ሲል አትቷል፡፡

 

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.