Fana: At a Speed of Life!

የሰሞኑ ጭጋጋማ አየር ከትንበያው አንጻር የሚጠበቅ ነው – ብሔራዊ ሚቲዮሮሎጂ ኤጀንሲ

አዲስ አበባ ፣ሐምሌ 21፣ 2013 ( ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ሰሞኑን እየታየ ያለው ጭጋጋማ አየር ከክረምቱ የአየር ትንበያ አንጻር የሚጠበቅ እንደሆነ ብሔራዊ ሚቲዮሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ።

በጭጋጋማው አየር የሚከሰተው የእይታ መጋረድ ጉዳት እንዳያስከትል ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም አሳስቧል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ በክረምት ዝናብ ተጠቃሚዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ ሊመዘገብ እንደሚችል ኤጀንሲው በትንበያው ማመላከቱን ገልጸዋል።

በተለይም የምስራቅ አጋማሽ በሚል የሚጠሩ አካባቢዎች በአብዛኛው መደበኛና በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ ከመደበኛ በላይ ዝናብ ሊያገኙ እንደሚችሉ መተንበዩን ተናግረዋል።

ከዚህ አኳያ ሰሞኑን የተከሰተው ጭጋጋማ የአየር ሁኔታ በአብዛኛው የክረምት ተጠቃሚ በሆኑ አካባቢዎች የታየና በክረምቱ ወቅት የሚጠበቅ ክስተት መሆኑ ግንዛቤ መወሰድ አለበት ብለዋል።
ጭጋጋማ አየር በኢትዮጵያ ለአጭር ጊዜ በሐምሌና በነሐሴ ወራት የሚታይ ነው፥ የአየር ሁኔታው “ዘላቂነት ላይኖረው ይችላል” ነው ያሉት አቶ ፈጠነ።

የዚህ አይነት ጭጋጋማ የአየር ሁኔታ እይታን የሚጋርድ እንዲሁም እይታዎች በአጭር ርቅት የተገደቡ እንዲሆኑ የሚያደርግ እንደሆነ ገልጸው፥ የእይታ መጋረድ በአየርና በየብስ ትራንስፖርት ላይ ተጽእኖ የሚያደርስ በመሆኑ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።

የብሔራዊ ሜቲዮሮሎጂ ኤጀንሲ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕና ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ጋር በቅንጅት በመስራት ጭጋጋማው አየር ከአየር ትራንስፖርት ጋር የሚኖረውን ተጽእኖ አስመልክቶ ዕለታዊ መረጃዎችን ለተቋማቱ እየሰጠ እንደሆነም ነው አቶ ፈጠነ ያስረዱት።

የሚሰጡትን መረጃዎች መሰረት በማድረግ ተቋማቱ እርምጃ እየወሰዱ ይገኛሉያሉት ዳይሬክተሩ፥ በየብስ ትራንስፖርትም አሽከርካሪዎችና መንገደኞች ለአደጋ እንዳይጋለጡ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ከጭጋጋማው አየር በተጨማሪ ከመደበኛ በላይ ዝናብ በሚጥልባቸው አካባቢዎች የጎርፍ አደጋን ለመከላከል ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

በተለይም የሚዘንበው ዝናብ በግብርና ምርቶች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ በማሳ ላይ የሚንሳፈፈውን ውሃ የማጠንፈፍና የውሃ ቦይ መቅደድ እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።

በከተሞች የጎርፍ ማስወገጃ ቱቦዎችን መጥረግና የጎርፍ ማሳለጫ መንገዶች ማበጀት እንደሚገባና ከተማ አስተዳደሮች ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት እንደሚጠበቅባቸውም ነው የተናገሩት።

ለጎርፍ ተጋላጭ በሆነ ረባዳማ መሬት ላይ የሚኖሩ ዜጎች በዝናብ ምክንያት አደጋ እንዳይደርስባቸው ድጋፍ ማድረግና ዜጎችም ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው መምከራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

የጎርፍ አደጋ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች በተለይም በተፋሰሶች የጎርፍ ቅድመ መከላከል ስራዎች ማከናወን እንደሚገባ የገለጹት ዳይሬክተሩ፥ በዚህ ረገድም ከሚመለከታቸው ሴክተር መስሪያ ቤቶች ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በክረምቱ እየጣለ ያለው ዝናብ ሊያደርስ የሚችለውን አሉታዊ ጉዳት በመቀነስ ዝናቡ የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች መጠቀም ላይ በትኩረት መስራት ይገባልም ነው ያሉት።

በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አካባቢ በተፈጠረ አስቸጋሪ የአየር ጸባይ ወደ አዲስ አበባ የሚደረጉ በረራዎች በአቅራቢያ በሚገኙ አውሮፕላን ማረፊያዎች እንዲያርፉ እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ መግለጹ ይታወሳል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.