Fana: At a Speed of Life!

ባለፉት ሁለት ሳምንት ከሳዑዲ አረቢያ እና ሌሎች ሃገራት 41 ሺህ በላይ ዜጎች ተመልሰዋል – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 22 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ሁለት ሳምንት ከሳዑዲ አረቢያ እና ሌሎች ሃገራት 41 ሺህ 485 ዜጎችን ወደ ሃገር መመለስ መቻሉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ መንግስት በሳዑዲ አረቢያ እና በሌሎች ሃገራት የሚገኙ ዜጎችን የመመለስ ፍላጎትና ዝግጁነት አለው ብለዋል፡፡
12 የፌደራል አካላት የተካተቱበት ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ ተመላሾችን ከቤተሰባቸው ጋር የማገናኘት ተግባር እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፥ የኪስ ገንዘብና የትራንስፖርት ወጪ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ለተመላሾቹ በአዲስ አበባ በተዘጋጁ ሶስት ጊዜያዊ መጠለያዎች ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን አንስተው፥ የፌደራል የስራ እድል ፈጠራ ኮሚሽንም የስራ እድል ለማመቻቸት ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን አስረድተዋል፡፡
ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው 60 ሺህ ያህል ዜጎች አሁንም በሳዑዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙም አውስተዋል፡፡
ከጎረቤት ሃገራት ጋር በተያያዘም ከጂቡቲ ጋር ያለው ግንኙነት ሰላማዊ መሆኑን ጠቁመው፥ በአንጻሩ ሱዳን በያዘቻቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች መንገድን ጨምሮ ሌሎች መሰረተ ልማቶችን እየገነባች መሆኑን ገልጸዋል፡፡
መንግስትም ይህ አካሄድ እንደማያዋጣ ለሱዳን ማስጠንቀቂያ እየሰጠ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ከሱዳን የድንበር ጉዳይ፣ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ እና ከትግራይ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ጉዳዮችን ኢትዮጵያ በንቃት እየተከታተለች መሆኑን በማንሳትም ነገሮች እየከሰሙ እንደሚሄዱ አመላክተዋል፡፡
መከላከያም በየትኛውም የድንበር አካባቢ ሊቃጡ የሚችሉ ትንኮሳዎችን ለመመከት ዝግጁ መሆኑንም ነው የገለጹት።
አሜሪካ ከኤርትራ ስደተኞች ጋር ተያይዞ በህወሓት ላይ ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክት ማስተላለፏ ሃገሪቱ ከዚህ ቀደም የያዘችውን አቋም እያሻሻለች መምጣቷን ያሳያልም ነው ያሉት፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞም መሰል መልዕክቶች ከሌሎች አካላት ይተላለፋሉ ተብለው እንደሚጠበቁም ነው ያነሱት፡፡
የተባበሩት መንግስታት የፖለቲካ እና የሰላም ግንባታ ጉዳዮች ሀላፊ ሮዝመሪ ዲካርሎ ኢትዮጵያ ለዜጎች ደህንነት ቅድሚያ በመስጠት የተናጥል ተኩስ አቁም ማወጇን አድንቀው ድርጅታቸው የኢትዮጵያን የልማትና የሰላም ጥረት እንደሚደግፍ መግለጻቸውንም አንስተዋል፡፡
ከአልሸባብ ጋር በተያያዘም ቡድኑ አሁንም አልፎ አልፎ የሚንቀሳቀስ አሸባሪ ሀይል እንጅ የኢትዮጵያ ስጋት አለመሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡
በወንድወሰን አረጋኸኝ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.