የበረሃ አንበጣው ቋሚ እና የመስኖ ሰብሎች ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል ተባለ
አዲስ አበባ ፣ ጥር 22 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ግብርና ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ እየተስፋፋ የሚገኘውን የበረሃ አንበጣ መቆጣጠር ካልተቻለ ቋሚ እና የመስኖ ሰብሎች ላይ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ገለፀ።
የግብርና ሚኒስቴር የእጽዋት ጥበቃ ዳይሬክተር ዘብዲዮስ ሰላቶ በሄሎኮፕተር የታገዘ እና በባህላዊ መንገድ እየተሰራ ያለው የመከላከል ስራ በሚፈለገው ፍጥነት እየሄደ አለመሆኑን ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።
የበረሃ አንበጣ ባለፉት ወራት በአፋር፣ ሰሜን ምስራቅ አማራ፣ ደቡብ ትግራይ፣ ምስራቃዊ ሶማሌ እና ኦሮሚያ፣ ምእራብ እና ምስራቅ ሀረርጌን ጨምሮ እስከ ድሬዳዋ ድረሰ ጉዳት አድርሷል።
አሁን ደግሞ በኦሮሚያ ክልል የባሌ፣ ቦረና እና ጉጂ ቆላማ አካባቢዎች እንዲሁም በደቡብ ክልል በመስፋፋት ሌላ ስጋት ፈጥሯል።
በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ ከተዛመተ ደግሞ ቋሚ ሰብሎች እና የመስኖ ውጤቶች ላይ ከፍተኛ ውድመት እንዳያስከትል ተሰግቷል።
ከደቡብ ኦሮሚያ የተነሳው የበረሃ አንበጣ አሁን ላይ በምስራቅ ሸዋ፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ አርሲ በከፊል እና ሞጆን ጨምሮ በሌሎችም የክልሉ አካባቢዎች በፍጥነት ተዛምቷል።
በክልሉ እርሻ እና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ የእጽዋት ጥበቃ ዳይሬክተሩ ደጀኔ ሂርጳ አሁን በክልሉ ከመስኖ ምርት በዘለለ የመኸር ሰብሎች የተሰበሰበበት ወቅት ቢሆንም ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ ይጠይቃል ብለዋል።
በደቡብ ክልልም ባለፉት 20 ቀናት በቡርጂ፣ አማሮ እና ያቤሎ በኩል የገባና በክልሉ 7 ዞኖች ተከስቶ የነበረውን የአንበጣ መንጋ የመከላከል ተግባሩ ቀጥሏል ተብሏል።
የክልሉ እርሻ እና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ የአዝዕርት ሰብሎች ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክተር ወንድማገኝ ሀይለማርያም መንጋውን በሄሊኮፕተር በመታገዝ እና በህዝቡ ተሳትፎ በተደረገ ርብርብ አሁን ላይ የመከላከል እርምጃው ውጤት እያመጣ መሆኑን አንስተዋል።
ይሁን እንጅ በቅርቡ ከኬንያ እና ሶማሊያ የተነሳው መንጋን ከወዲሁ መቆጣጠር የማይቻል ከሆነ አሁንም ክልሉን መዳረሻው ማድረጉ አይቀርም ብለዋል።
አሁን ላይ እየተካሄደ ያለው የኬሚካል ርጭት ባለፈም አንበጣውን በመግደል ቁጥሩን የመቀነስ ስራዎች ሊሰሩ ይገባልም ነው ያሉት።
በአፈወርቅ አለሙ