3 ሺህ 700 ሰዎችን በያዘችው መርከብ ላይ አዲስ 41 የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ተገኙ
አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በጃፓን የባህር ዳርቻ መልህቋን በጣለችው መርከብ ላይ በኮሮና ቫይረስ የተጠቁት ሰዎች 61 ደረሰ።
3 ሺህ 700 ሰዎችን የያዘችው ዳይመንድ ፕሪንስስ መርከብ ላለፉት ሁለት ሳምንታት በዮኮሀማ ለይቶ ማቆያ አካባቢ ትገኛለች።
በመርከቧ ውስጥ በቫይረሱ ተጠቅተው ከነበሩ 19 ሰዎች በተጨማሪ አዳዲስ 41 የቫይረሱ ተጠቂዎች መገኘታቸውን ተከትሎ በጃፓን በቫይረሱ የተጠቁት ሰዎች 86 ደርሰዋል።
ምርመራ ከተደረገላቸው 171 ሰዎች መካከል 41ዱ በቫይረሱ መጠቃታቸውን የጃፓን ጤና ሚኒስትር ካትሱኖቡ ካቶ አረጋግጠዋል።
ጃፓን ባለፈው ወር በመርከቧ ላይ የነበሩና የሆንግ ኮንግ ነዋሪ የሆኑ የ80 አዛውንት በቫይረሱ መጠቃታቸው ይፋ መሆኑን ተከትሎ በዳይመንድ ፕሪንስስ መርከብ ላይ በነበሩ ተሳፋሪዎች ላይ ምርመራ መጀመሯ ይታወሳል።
አዛውንቱ በፈረንጆቹ ጥር 20 ቀን 2020 በመርከቧ ተሳፍረው ጥር 25 ቀን ከመርከቡ መውረዳቸው ነው የተነገረው።
ከዚህ ባለፈም ዎርልድ ድሪም በተሰኘች ሌላ መርከብ ላይ የነበሩ ስምንት ሰዎች በቫይረሱ መጠቃታቸው በመረጋገጡ መርከቧ በሆንግ ኮንግ በለይቶ ማቆያ አካባቢ እንድትቆይ ተደርጋለች።
መርከቧ ውስጥ በሚገኙ ሰዎች ላይ በተካሄደው ምርመራው በቫይረሱ የተጠቃ ሰው አልተገኘም።
በሌላ ዜና በኮሮና ቫይረስ አደገኛነት ዙሪያ ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ የነበረው ዶክተር ሊ ዌንሊያንግ ህይወቱ አልፏል።
ዶክተር ሊ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎችን ሲያክም በቫይረሱ ተጠቅቶ ህይወቱ ሊያልፍ ችሏል።
የስራ ባልደረቦቹን ስለ ቫይረሱ አደገኛነት እያስጠነቀቀ የነበረው ዶክተር በወቅቱ ፖሊስ ሀሰተኛ አስተያየት አትስጥ በሚል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት ነበር።
የዶክተሩ ህልፈት በቻይናውያን ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን መቀስቀሱ ነው የተገለፀው።
ምንጭ፦ ቢቢሲ
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision