Fana: At a Speed of Life!

ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም የምስክርነት ጥበቃቸው ተነስቶ ዳግም ፍርድ ቤት ቀረቡ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 19 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የቀድሞዋ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም የምስክርነት ጥበቃቸው ተነስቶ ዳግም ፍርድ ቤት መቅረባቸውን ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ገለጸ።

ወይዘሮ ኬሪያ ዛሬ የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርበዋል።

የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ አወል ሱልጣን ለኢዜአ እንደገለጹት÷ ወይዘሮ ኬሪያ ከተከሳሽነት ወደ ምስክርነት ተቀይረው ነበር።

ተጠርጣሪዋ በጠቋሚዎችና ምስክሮች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/2003 በገቡት ሥምምነት መሠረት ዝርዝር የምስክርነት ቃላቸውን በፈቃዳቸው መስጠታቸውን አስታውሰዋል።

በገዛ ፈቃዳቸው በጽሑፍና በሲዲ ምስክርነታቸውን ሰጥተው እንደነበር ያስታወሱት አቶ አወል በፍርድ ቤት ውሳኔ ከእስር እንደተለቀቁና ጎን ለጎንም ለግለሰቧ አስፈላጊውን የምስክርነት ጥበቃ ሲደረግላቸው መቆየቱን ተናግረዋል።

ይሁንና ወይዘሮ ኬሪያ ቆይተው ምስክር የመሆን ፍላጎት እንደሌላቸው እንዲሁም ምስክርነት ሲሰጡ የቆዩት ተገደው እንደነበር በመግለጻቸው ምስክረነታቸው መቋረጡን ገልጸዋል።

በምስክሮችና ጠቋሚዎች አዋጅ ቁጥር 699/2003 አንቀጵ 11 መሰረት የጥበቃ ተጠቃሚው ሥምምነቱንና ግዴታውን የማያከብር ከሆነ የጥበቃ ስምምነት ውሉ ስለሚቋረጥ አቃቤ ሕግም ለወይዘሮ ኬሪያ ምስክር በመሆናቸው ይሰጣቸው የነበረውን ጥበቃ ለማንሳት መገደዱን ነው አቶ አወል የተናገሩት።

“ከዚህም በኋላ ወይዘሮ ኬሪያ ከዚህ ቀደም በተጠረጠሩበት ወንጀል የቅድመ ምርመራ ስራ እንዲጀመር አቃቤ ሕግ ዛሬ ለፍርድ ቤት ጥያቄ አቅርቧል” ብለዋል።

የተጠርጣሪዋ ጠበቆች በጉዳዩ ላይ ለመከራከር አልተዘጋጀንም በማለታቸው ፍርድ ቤቱ ወይዘሮ ኬሪያ በመጪው ሰኞ ዳግም ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ አዟል።

ወይዘሮ ኬሪያ እስከ መጪው ሰኞ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንዲቆዩም ፍርድ ቤቱ ወስኗል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.