በጋምቤላና በኦሮሚያ ህዝቦች መካከል የአብሮነት እሴትን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላና በኦሮሚያ ክልል ህዝቦች መካከል ያለውን የአብሮነት እሴቶች በማጠናከር ሰላምን በዘላቂነት ማስቀጠል እንደሚገባ ተገለፀ።
በጋምቤላ እና በኦሮሚያ ክልሎች አጎራባች ዞን፣ ወረዳ እና ቀበሌዎች የተዘጋጀ የሰላም ኮንፈረንስና የምክክር መድረክ በጋምቤላ ከተማ ተካሂዷል።
የጋምቤላ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ አኳይ ኡጁሉ በወቅቱ÷ የጋምቤላ እና የኦሮሚያ ክልል ህዝቦች ለዘመናት የዘለቀ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት አላቸው ብለዋል።
በሁለቱ ህዝቦች መካከል ያለውን አንድነትና ወንድማማችነት በማጠናክር ድህነትና ኋላ ቀርነት ላይ መዝመት እንደሚገባቸው አመላክተዋል።
በሁለቱ ክልሎች መካከል ያለውን ትስስር በማጠናከር ህዝቡን በሠላምና በልማት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል።
የኦሮሚያ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ጋምቤላ ክልሎች የጋራ የሰላም እና ልማት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፊሮምሳ ሰለሞን በበኩላቸው÷ የሁለቱ ክልሎች ህዝቦች በደስታም ሆነ በችግር ለዘመናት አብረው መኖራቸውን አስታውሰዋል።
መድረኩ በሁለቱ ህዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነትና አንድነት ለማጠናከር የጋራ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን ለማጠናከር ያለመ እንደሆነም ገልፀዋል።
የህብረተሰቡን አንድነት የበለጠ ለማጠናከር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም መግለጻቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
በመድረኩ በሁለቱ ክልሎች አጎራባች ዞን፣ ወረዳና ቀበሌዎች የሚገኙ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡