Fana: At a Speed of Life!

ደቡብ ኮሪያ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን የሰብዓዊ ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ደቡብ ኮሪያ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን የሰብዓዊ ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጻለች፡፡

በቅርቡ የተሾሙት በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ጃንግ ካንግ እንዳሉት÷ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ኮሪያ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት አላቸው፡፡

ሀገራቱ በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ያላቸው ትስስር ጠንካራ መሆኑን ጠቁመው÷ ለዚህም ኢትዮጵያ በኮሪያ ጦርነት ወቅት ለደቡብ ኮሪያ ያደረገችው እገዛ ጠንካራ መሰረት መጣሉን አስታውሰዋል፡፡

የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ይበልጥ ለማጠናከርም የኮሪያ የባህል ልዑካን ከኢትዮጵያ አቻቸው ጋር የልምምድ ልውውጥ የሚያደርጉበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ገልጸዋል።

በቀጣይ ሀገራቱ በተለያዩ ዘርፎች ያላቸውን ሁለንተናዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስም በትብብርና በትኩረት እንደሚሰሩ አምባሳደሩ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ የጀመረችውን የልማት ሥራ ለመደገፍም ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት አስፈላጊው ትብብትር እንደሚደረግ አንስተዋል፡

ኢትዮጵያ ከደቡብ ኮሪያ የሰብዓዊ ድጋፍ በማግኘት ከአፍሪካ ቀዳሚ መሆኗን የጠቆሙት አምባሳደሩ÷ በቀጣይም ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

በርካታ የኮሪያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እያደረጉ መሆኑን ገልጸው÷ ሌሎች ባለሃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱም በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.