ከወጪ ንግድ ምርቶች ከ600 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በበጀት ዓመቱ 8 ወራት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ክትትል ከሚያደርግባቸው የወጪ ንግድ ምርቶች 617 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን አስታወቀ፡፡
በስምንት ወሩ ከወጪ ንግድ 705 ነጥብ 15 ሚሊየን ዶላር ለማግኘት የተያዘው ዕቅድ 87 ነጥብ 51 በመቶ መፈጸሙን ገልጿል፡፡
ገቢው ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት አፈፃጸም ጋር ሲነፃጸርም የ80 ነጥብ 08 ሚሊየን ዶላር ወይም 14 ነጥብ 91 በመቶ ብልጫ እንዳለውም ነው የተነገረው፡፡
የጥራጥሬ እና የቅባት እህሎች ደግሞ ከፍተኛውን ገቢ ያስገኙ ምርቶች ናቸው መባሉን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የውልና ኢንቨስትመንት እርሻ መመሪያ ተግባራዊ መደረጉ፣ የአኩሪ አተር፣ ቀይ ቦሎቄና ማሾ ምርቶች ዓለም አቀፍ ገበያ ፍላጎት መሻሻሉ እንዲሁም የሰሊጥ ምርት መጨመር በዘርፉ ለተገኘው ውጤት ማደግ ተጠቃሽ ምክንያቶች እንደሆኑም ተጠቁሟል፡፡