Fana: At a Speed of Life!

የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለሁለንተናዊ ብልጽግና በሚል የውይይት መድረኮች ሊካሄዱ ነው

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 10 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በሴቶች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች በየደረጃው እንዲፈቱ ለማድረግ እና በቀጣይ በሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ሴቶች ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማስቻል “የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል ርዕስ እስከ ቀበሌ ድረስ የንቅናቄ መድረኮች ሊካሄዱ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ወይዘሮ መስከረም አበበ የሚፈጠረው መድረክ የሴቶችን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ በሚደረገው ጉዞ ውስጥ እንቅፋት የሚሆኑ ችግሮችን በመለየትና በግልጽ በመነጋገር በየደረጃው ችግሮች እየተፈቱ እንዲሄዱና ሴቶች ላይ መነቃቃት በመፍጠር በአጠቃላይ የበለጸገች ህብረ ብሔራዊት ሀገር በመገንባት ሂደት ውስጥ የሴቶችን ሚና ለማሳደግ ታሳቢ ያደረገ መድረክ ነው ብለዋል፡፡

ሀላፊዋ አያይዘውም መድረኩ በክልል ደረጃ የሚጀምርና የዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ የህግ ባለሙያዎች፣ የመንግስት ሰራተኞችና ሌሎችም ሴቶች የሚሳተፉበት መሆኑን ጠቅሰው በቅርቡ በሚካሄደው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ እንደ ፓርቲ 50 በመቶ ሴቶች ዕጩ ሆነው እንዲቀርቡ መወሰኑን አውስተዋል፡፡

በጽህፈት ቤቱ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪክ ማህበራት ዘርፍ ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር አለሙ ስሜ በበኩላቸው፥ የሴቶችን ዘላቂ ችግር ለመፍታት ሴቶች ተደራጅተው መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

ሴቶችን የማብቃት፣ የማሰልጠንና የማዘጋጀት ስራ ከልዩ ልዩ ተቋማት ጋር በቅንጅት መስራት ያስፈልጋልም ማለታቸውን ከፓርቲው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ሚኒስትሩ አያይዘውም ሴቶችን በምንም መንገድ ሊገድቡ የሚችሉ አመለካከቶችን መታገል እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፥ ለሴቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት መታገልና በቅርቡ ለሚካሄደው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ 50 በመቶ ዕጩ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እንደ ፓርቲ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.