Fana: At a Speed of Life!

ፊቤላ ኢንዱስትሪ ከ12 ሚሊየን ሊትር በላይ ዘይት ለገበያ ማቅረቡን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 4፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ፊቤላ ኢንዱስትሪ ከ12 ሚሊየን ሊትር በላይ ዘይት ለገበያ ማቅረቡን የፊቤላ ኢንዱስትሪ ባለቤትና የቢኬጂ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ በላይነህ ክንዴ አስታወቁ።

ከዚህ ውስጥ ስምንት ሚሊየን የሚጠጋውን በአከፋፋዮች አማካኝነት ለህዝብ መሰራጨቱንም አመልክተዋል።

የአከፋፋዮች እጥረት እንደነበረ የገለጹት አቶ በላይነህ መንግሥት በሃገር አቀፍ ደረጃ 33 አከፋፋዮች ወደ ስራው እንዲገቡ ማድረጉንም ጠቅሰዋል፡፡

ድርጅታቸው በመጀመሪያው ዙርና በሁለተኛው ዙር በተፈቀደለት የውጭ ምንዛሪ 34 ሚሊየን ሊትር ድፍድፍ ዘይት ከውጪ ማስገባቱን አስታውሰዋል፡፡

ፊቤላ እስካሁን ድረስ አንድ ሊትር ከ39 ነጥብ 5 እስከ 42 ብር ለአከፋፋዮች እያቀረበ ይገኛል፡፡

ይህ ዋጋ በዓለም ላይ አንድ ሊትር ዘይት ከሚሸጥበት ዋጋ በእጅጉ ያነሰ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት የዓለም አቀፍ የድፍድፍ ዋጋ ከፍ በማለቱ እና የዶላር ዋጋ በመናሩ፤ በነበረው ዋጋ ለማቅረብ አስቸጋሪ ነው ያሉት አቶ በላይነህ፤ ከዚህ አኳያ የዋጋ ማስተካከያ ለማድረግ አዲስ የትመና ዋጋ እየተሠራለት ነው ብለዋል።

ከጥራት ጋር ተያይዞም የፊቤላ ዘይት ቀደም ሲል ከውጭ ሃገር ታሽጎ ከሚመጣው ዘይት በተሻለ የፋት አሲድን በመቀነስ ለተጠቃሚዎች ምቹ እንዲሆን ተደርጎ እየቀረበ መሆኑን አመልክተዋል።

ፋብሪካው በቀን አንድ ሚሊየን ሊትር ዘይት የማምረት አቅም እንዳለው ያመለከቱት አቶ በላይነህ 6 ሺህ 500 ኪሎ ዋት የሚያመነጩ ትላልቅ ጄኔሬተሮች በመገዛታቸው በቅርብ ቀናት ውስጥ ፋብሪካው 24 ሰዓት ማምረት ያስችለዋል ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.