ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ከቻይና እና አሜሪካ አምባሳደሮች ጋር ተወያዩ
ርዕሰ መስተዳደሩ ዶክተር ይልቃል ከፋለ በውውይቱ ላይ ባድረጉት ንግር፥ አሸባሪው የህውሓት ቡድን በአማራ ክልል ወረራ ባካሄደበት ወቅት በርካታ መሰረተ ልማቶችን ያወደመና የዘረፈ መሆኑን አስረድተዋል።
አሁን ላይ የወደሙና የተዘረፉ መሰረተ ልማቶችና ተቋማትን መልሶ ለመገንባት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፥ የቻይና መንግስትም የቆየውን ወዳጅነትና የልማት አጋርነት አጠናክሮ በማስቀጠል በመልሶ ግንባታ ስራዎች ላይ የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ርዕሰ መስተዳደሩ ጠይቀዋል።
ዶክተር ይልቃል በህወሓት አሸባሪ ቡድን ወረራ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው የቻይና ፕሮጀክቶችን መልሰው እንዲቋቋሙና ወደ ስራ እንዲገቡ የክልሉ መንግስት በትኩረት እንደሚሰራም ገልጸው፥ የቻይና መንግስት ለአማራ ክልል የሚያከናውነውን ልማታዊ እንቅስቃሴ አጠናክራ እንዲቀጥልም ነው የጠየቁት፡፡
በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዛዎ ችዩዋን በበኩላቸው፥ ቻይና ከአማራ ክልል የመንግስት መዋቅር ጋር በቅርበትና በትብብር እየሰራች መሆኑን ጠቁመው፥ የሀገራቱ የጠበቀ ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ያላቸውን እምነት መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ውይይቱ በክልሉ ወቅታዊ ሁኔታና ዘላቂ ልማት ላይ ያተኮረ ሲሆን÷ በተለያዩ ስፍራዎች ጉብኝት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡