አሜሪካ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትስስር ማጠናከር ትፈልጋለች-ትሬሲ ጃኮብሰን
አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ በኢኮኖሚና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትስስር ማጠናከር ትፈልጋለች ሲሉ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ጉዳይ አስፈጻሚ አምባሳደር ትሬሲ አን ጃኮብሰን ተናገሩ፡፡
ለስራ ጉብኝት ጅማ ከተማ የሚገኙት ትሬሲ ጃኮብሰን÷ በከተማዋ እና አካባቢው ያሉ ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታዎችን በተመለከተ ገለጻ ተደርጎላቸዋል።
ትሬሲ ጃኮብሰን በጅማ ዞንናበኦሮሚያ ክልል አመቺ የቡና ልማት መኖሩን ጠቅሰው÷ ሀገራቸው በኢኮኖሚና በኢንቨስትመንት ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትስስር ማጠናከር እንደምትፈልግ ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል ያለው የሰላም ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱንና ለዚህም አሜሪካ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ ተናግረዋል።
በኮቪድ-19 ምክንያት ለሁለት ዓመታት ተዘግቶ የቆየው አሜሪካን ኮርነር ቤተመጽሓፍ በአምባሳደሯ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚደረግ ተመላክቷል
በሙክታር ጣሃ