Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ አቡዳቢ ገብተዋል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አቡዳቢ ገብተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቡዳቢ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼህ አብደላ ቢን ዛይድ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለሶስት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ዛሬ ወደ ተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች ማቅናታቸው ይታወሳል።

በቆይታቸውም በሀገሪቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን መብት እና ጥቅም የሚያስከብሩ ውይይቶችን እንደሚያደርጉ የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

በቆይታቸው ከ15 ሺህ ኢትዮጵያውያን ጋር የሚወያዩ ሲሆን፥ ዜጎች ክብራቸው ተጠብቆ፣ መብታቸው ተከብሮ፣ ጥቅማቸው ተረጋግጦ እና በማንነታቸው ኮርተው እንዲኖሩ የሚያስችሉ ውይይቶችን ከዜጎች እና ከመሪዎች ጋር እንደሚያደርጉም መናገራቸውም ይታወሳል።

አቶ ንጉሱ ትናንት በሰጡት መግለጫ ዜጎች ህጋዊነትን በተላበሰ ሁኔታ እንዲሰማሩ ከማድረግ ባሻገር የህግ ስምምነቶችን ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ጋር መከናወኑን ጠቅሰዋል።

በዚህም እስካሁን ድረስ ከዮርዳኖስ፣ ኳታር፣ ሳዑዲ ዓረቢያ እና ከተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች ጋር ስምምነት መደረሱን አስረድተዋል።

መንግስት በአሁኑ ወቅት በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ዙሪያ ትኩረት በማድረጉ እስካሁን ከ100 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውንም በመግለጫቸው አስታውሰዋል።

በዓላዛር ታደለ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.