Fana: At a Speed of Life!

በቻድ መፈንቅለ መንግስት ከተደረገ 3 ዓመታት በኋላ ምርጫ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቻድ መፈንቅለ መንግስት ከተካሄደ ሶስት ዓመታት ቆይታ በኋላ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እየተካሄደ ነው፡፡

በዚህም ቻድ በሳህል ቀጣና መፈንቅለ መንግስት ከተደረገባቸው ሀገራት ምርጫ ያካሄደች የመጀመሪያዋ ሀገር መሆን ችላለች፡፡

ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫው 8 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች የተመዘገቡ ሲሆን ፥በሀገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ከጠዋቱ 1 ሰዓት እስከ 11 ሰዓት እንደሚቆይ ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል የሀገሪቱ ወታደሮች በትናንትናው ዕለት ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫው ድምጽ መስጠታቸው ነው የተገለጸው፡፡

የፕሬዚዳንታዊ ምርጫው ጊዜያዊ ውጤት በፈረንጆቹ ግንቦት 21 እና የመጨረሻው ውጤት ደግሞ እስከ ሰኔ 5 ቀን ይፋ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡

የምርጫ ተወዳዳሪ እጩዎቹ መካከል ከ50 በመቶ በላይ ድምጽ ካልተገኘ ሁለተኛ ዙር ምርጫ በፈረንጆቹ ሰኔ 22 እንደሚካሄድም ተጠቁሟል፡፡

ከእጩዎቹ መካከል ለ30 ዓመታት የመሩት አባታቸው ኢድሪስ ዴቢን በፈረንጆቹ ሚያዝያ 2021 በመፈንቅለ መንግስት ከተገደሉ በኋላ የሽግግር ፕሬዚዳንት ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት ማሃማት ኢድሪስ ዴቢ አንዱ ናቸው፡፡

ዴቢ በሀገሪቱ ደህንነትን እና የሕግ የበላይነትን ለማጠናከር እንዲሁም የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ለማሳደግ ቃል ገብተዋል፡፡

በአንጻሩ ተቀናቃኛቸው ሰክሰስ ማሳራ እንደ መብራት፣ ውሃ እና በደህንነት ዙሪያ ላሉ አስቸኳይ ችግሮች መፍትሄ እንደሚያመጡ ተናግረዋል፡፡

ቻድ ከመፈንቅለ መንግስት በኋላ ለሦስት ዓመታት በወታደራዊ አገዛዝ ሥርዓት ስትተዳደር መቆየቷን ሬውተርስ እና አፍሪካ ኒውስ ዘግበዋል፡፡

በሳህል ቀጣና መፈንቅለ መንግስት አካሂደው እስካሁን ምርጫ ካላካሄዱ ሀገራት መካከል ማሊ፣ ቡርኪናፋሶ እና ኒጅር አንደሚገኙበት መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.